የኢትዮጵያ ሶሻል ኢንተርፕራይዝ ፎረም (ESEF) ታህሳስ 2 ቀን 2016 (እ. ኤ. አ.) ሁለተኛ ዝግጅቱን በብሪቲሽ ካውንስል ግቢ ውስጥ አካሂዷል። "ራስን እና የፈጠራ ሃሳብን ማስተዋወቅ የሚቻልበት መንገድ” በሚል ርእስ ሪች ፎር ቼንድጅ ኢቲዮፒያ
ያስጀመረውና የሚመራው የኢትዮጵያ ሶሻል ኢንተርፕራይዝ ፎረም የተዘጋጀው፣ በታህሳስ ወር አጋማሽ ላይ የተከበረውን የ2016ቱን (እ. ኤ. አ.) ዓለም አቀፍ የሥራ ፈጣሪዎች ሳምንትን ምክንያት በማድረግ ሲሆን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ዓለም አቀፋዊ የማኅበራዊ ተቋም እንቅስቃሴ ግንዛቤ የማስጨበጥ አላማ ነበረው። በዝግጅቱ ላይ 50 ጠንካራ ማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰቡ እና የመንግሥታዊ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተው ነበር። ዝግጅቱ አሳታፊ የሆነ እና ህያው ነበር፤ እንዲሁም ሁለት ግሩም ተጋባዥ ተናጋሪዎች ነበሩ። እነርሱም የጠብታ የአምቡላንስ አገልግሎት መስራች የሆኑት ክብረት አበበ እና ለህዝብ ንግግር የማቅረብ አስደናቂ ችሎታ ያላቸው እና የቶስትማስተርስ ኢን ኢቲዮፒያ መስራች የሆኑት ወንድወሰን ገብረ እግዚአብሄር ናቸው። ክብረት፣ የበርካቶችን ሕይወት ማትረፍ የሚያስችል ሥራ በመሥራታቸውና የሌሎችን አስተሳሰብ በመማረክ የሚታወቁት የኢትዮጵያን የማኅበረሰባዊ ሥራ ፈጠራ ሽልማትን ያሸነፉ የተከበሩ ሰው ናቸው።
ይህ ሁለተኛ ዝግጅት፣ ፎረሙ ከተመሰረተበት እ. ኤ. አ. ከመስከረም 2016 ወዲህ ተሳታፊዎቹ ራሳቸውን እና የፈጠራ ሃሳባቸው ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተዋወቅ የሚያስችሉ ክህሎቶችን እና ዘዴዎችን ያወቁበት ጠቃሚ መድረክ እንደነበረ ገልፀዋል። በፎረሙ የታደሙ ሰዎች እና ተሳታፊዎቹ ያሳዩት ከፍተኛ መነሳሳት፣ ይህ ገና ለጋ የሆነ ፎረም በፍጥነት እንዳደገ እና በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪዎች እያበቡ እንዲሄዱ የሚያስችል ሁኔታ የመፍጠር አላማውን እያሳካ እንዳለ ያሳያሉ።