Tuesday 24 January 2017

ብሪቲሽ ካውንስል፣ አሥር የመንግሥት ባለሥልጣናትንና ፖሊሲ አርቃቂዎችን ያቀፈ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያንንና ኬንያውያንን ያካተተ የልዑካን ቡድን ከምሥራቅ አፍሪካ ወደ ዩናትድ ኪንግደም ሄዶ ከኅዳር 14-18, 2016 (እ. ኤ. አ.) በተካሄደ ታሪካዊ በሆነ ዓለም አቀፋዊ ትምህርታዊ ጉብኝነት ላይ እንዲሳተፍ ዝግጅት አድርጎ ነበር። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለምሳሌ፣ የኢንዱስትሪ፣ የትምህርት፣ የማኅበራት እንዲሁም የከተማና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን አሊያም በሥራቸው ያሉ ኤጀንሲዎችን ወክለው የመጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጉብኝቱ ላይ ተሳትፈዋል። በተጨማሪም የማኅበራዊ ተቋማት እና ለውጥ ፈጣሪ የሆኑ የባለ ሀብቶች ተቋማት መሪዎች በቡድኑ ውስጥ ይገኙ ነበር። ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የተውጣጣው የመጀመሪያው የልዑካን ቡድን የተገኘበት ስብሰባ፣ በአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ ለሚያገኘው ፖሊሲ አውጪዎችንና ፖሊሲ አርቃቂዎችን ላካተተው የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበራዊ ተቋማት ድጋፍ መስጫ (EU-funded Support for Social Enterprises in Eastern Africa) ፕሮጀክት አቅም የመገንባት ሥራ ለማከናወን ወሳኝ የሆነ ድርሻ ነበረው። ይህ የመጀመሪያው የአውሮፓ ሕብረት ጥናታዊ ጉብኝት፣ በኢትዮጵያና በኬንያ የአገር ውስጥ የማኅበራዊ ተቋማት ምህዳሮችን ለማጎልበት መንግሥታቱ የሚሰጡትን ድጋፍ የማጠናከር ፍላጎት እና ተነሳሽነት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ያስገኘው ውጤት ሲገመገም፣ ዝግጅቱ በእርግጥም ወሳኝ ሚና መጫወቱን ያሳያል።

ጥናታዊ ጉብኝቱ፣ እጅግ ጠቀሜታ ያላቸው ዓለም አቀፋዊ ማኅበራዊ ተቋማት ትስስር እንዲፈጠር እና የልምድ ልውውጥ የሚደረግባቸው አጋጣሚዎች እንዲከፈቱ የሚረዱ በርካታ ቁልፍ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን አካትቶ ነበር። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት ልዑካኑ በበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የጉድ ዲልስ 2016 (እ. ኤ. አ.) ኮንፈረንስና አውደ ርእይ ላይ ተገኝተው ነበር። ጥናታዊ ጉብኝቱ የጀመረው ከማኅበራዊ ተቋም፣ ከመዋእለ ንዋይ እና ከፈጠራ ሥራ አንፃር በዩናይትድ ኪንግደም ግንባር ቀደም በሆነው ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንስ ማለትም በጉድ ዲልስ መሆኑ የተገባ ነው፤ ይህ መሆኑ ልዑካኑ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፋዊ እውቀት ለማካፈል፣ ለመቅሰምና ወደ አገራቸው ይዘው ለመመለስ ላቅ ያለ የቁርጠኝነት ስሜትና ተሳትፎ የማድረግ ፍላጎት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ነበር። ልዑካኑ በዩናትድ ኪንግደም ላይ በሚያተኩሩ በርካታ ትምህርታዊ ስብሰባዎች ላይ ከቀረቡት ንግግሮችና ውይይቶች እንዲሁም በጉድ ዲልስ በሚገኘው አውደርዕይ ካደረጉት ጉብኝት ጠቃሚ ተሞክሮዎችንና ትምህርቶችን አግኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በመላው ዓለም በሚገኙ ሶሻል ኢንተርፕራይዞች ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን መሰረት ባደረገው ትምህርታዊ ስብሰባ አማካኝነት የመማር አጋጣሚ አግኝተዋል። ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ሥነ ማኅበረሰባዊ የሥራ ፈጠራ አሸናፊ የሆኑት ክብረት አበበ ያቀረቡት አሳማኝ የሆነ ጥናታዊ ጽሑፍ ይገኝበታል። ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ በምሥራቅ አፍሪካ ማኅበራዊ ተቋማት ስለሚገኙባቸው ተጨባጭ ሁኔታዎችና እውነታዎች ግንዛቤ በማስጨበጥም ሆነ ተመሳሳይ የሆኑ የመማር ሂደቶችን በማስጀመር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል። አንድ ልዑክ “መዋቅሩ እዚያው ባለበት እንዲቆም አታድርጉ፤ ይልቁንም ከተለያዩ ናሙናዎች እውቀት መቅሰማችሁን ቀጥሉ” የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል።

ልዑካኑ፣ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የሚሠሩ ስኬታማ የሆኑ በርካታ አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተቋማት ለአብነት ያህል፣ በዝቅተኛ ወጪ የሚካሄዱ የቤቶች ግንባታ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ለመስክ ጥናት መርጠው በቡድን ሆነው ጎብኝተዋል። በበርሚንግሃም ትሪደንት የተባለው ድርጅት የሚያከናውነው ሥራ እጅግ አስደንቋቸዋል፤ ድርጅቱ በመሃል አገር በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ 3,558 ቤቶችን የሚያስተዳድሩ የቤቶች ማኅበራት፣ የእርዳታ ተቋሞችና ማኅበራዊ ተቋሞች ስብስብ ነው። ለንደን ውስጥ ስለሚገኘው ኤችቲሲ (HTC) የተባለ የመጓጓዣ አገልግሎት መስጫ ስለሆነ ማኅበራዊ ተቋም እና ኃላፊነቱ ያልተወሰነ ማኅበራዊ ተቋም ስለሆነ አንድ የገበያ ቦታ አዲስ እውቀት አግኝተዋል። በተጨማሪም ታዋቂ ከሆኑ ከሌሎች ማኅበራዊ ተቋማት ለምሳሌ፣ ከብሪስተን ግሩፕ፣ ከሶፕ - ኮ፣ ከኮይን ስትሪት ኮሚውኒቲ ቢልደርስ የተገኘው ተሞክሮ በእጅጉ ግንዛቤ የሚያሰፋ ነው። ከዚህም ሌላ በሰዎችና በፕላኔቷ ላይ ተጽእኖ በመፍጠር ሥራ ላይ የሚሳተፍ እያደገ የመጣውን ኢምፓክት ሃብ የተባለውን ማኅበረሰባዊ ተቋም ጎብኝተዋል። በመስክ ጉብኝት የታዩት እንቅስቃሴዎች እጅግ ተጨባጭና አሳማኝ በመሆናቸው ልዑካኑ የማኅበራዊ ተቋማትን ምንነትና ያላቸውን አቅም በሚመለከት ግንዛቤያቸው በጣም ጨምሯል። አንድ ልዑክ ያዩትን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “ማኅበራዊ ተቋማት ከገንዘብም ሆነ ከማኅበራዊ ጉዳዮች አኳያ በገበያ ላይ የተመሠረቱ መፍትሔዎች እንደሚያስገኙ ማስረጃ አግኝተናል። እነዚህ ማኅበራት ውሎ አድሮ በዘላቂነት መቆምና ማኅበረሰባዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይችላሉ፤ ደግሞም እነዚህ ሁለት ነገሮች የሚነጣጠሉ አይደሉም።” ከሁሉም በላይ ደግሞ ልዑካኑ የተመለከቷቸው የተለያዩ ናሙናዎች በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር በተመሳሳይ መልኩ ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ደርሰውበታል። “ከቤቶች፣ ከመጓጓዣ፣ ወዘተ . . . ጋር በተያያዘ በአገሬ ሊሠራ የሚችል ነገር እንዳለ ማወቄ አስገርሞኛል። ይህም በአገሬ አንድ ልዑክ አማካኝነት አዳዲስ የሥራ መስኮችን በማፈላለግ ሌሎችን የማነሳሳት ፍላጎት አሳድሮብኛል” በማለት የተናገሩ ሲሆን አንድ ሌላ ልዑክ ደግሞ “በማኅበራዊ ተቋማት አማካኝነት የሥራ መስክ/የምጣኔ ሃብት እድገት ስለመፍጠር ጥሩ ሐሳቦችን እንደቃረሙ” በእርግጠኝነት ገልጸዋል።

ልዑካኑ ዘርፉን በተመለከተ በብሔራዊ ደረጃ በዩናይትድ ኪንግደም ስላለው የማኅበራዊ ተቋማት ምህዳር ይበልጥ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዲያገኙና የአገሪቱ መንግሥት የዘርፉን እድገት ለመደገፍ ስለሚጫወተው ሚና በቂ ትምህርት ለመቅሰም እጅግ የተሻለ አቋም እንዲኖራቸው አጋጣሚ የሚከፍቱ እንቅስቃሴዎች አድርገዋል። ከመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ለምሳሌ፣ በትምህርት ቁልፍ ቦታ ካላቸው ሌሎች ሰዎች ጋር ተገናኝተዋል። እነዚህ ስብሰባዎች ማኅበራዊ ተቋም በዩናትድ ኪንግደም የትምህርት ሥርዓትም ሆነ በሌሎች የእድገት ፕሮግራሞች እንዴት እንደተካተተ ለመረዳት ጠቃሚ ሆነው ተገኝተዋል። አንድ ልዑክ “በትምህርት ሥርዓቱና በማኅበራዊ ተቋማት እድገት መካከል ያለውን ቁርኝት” መረዳታቸው በጣም አስገርሟቸዋል። ሌላው ደግሞ “በሥርዓተ ትምህርት ዙሪያ የይዘት ለውጥ እንደሚያስፈልግ” ገልፀዋል። ልዑካኑ በሃውስ ኦፍ ሎርድስ ተገኝተው ከፓርላማ አባላት፣ ታዋቂ ከሆኑ የማኅበራዊ ተቋማት መሪዎችና ከሌሎች አካላት ጋር በደንቦች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። በተጨማሪም ልዑካኑ በዩናይትድ ኪንግደም ባለው የማኅበራዊ ተቋማት የሕግ አወቃቀር ዙሪያ ከታወቀ የዩኬ የእርዳታ ድርጅት የሕግ ተቋም ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል። እነዚህ ልዑካኑ ያከናወኗቸው ነገሮች፣ የወጡት ደንቦች እንዲሁም የሕግና የተቋም ማእቀፎች በዩናይትድ ኪንግደም ማኅበራዊ ተቋማትን ለመደገፍ ምን ድርሻ እንዳላቸውና እነዚህኑ በሌላ ቦታ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ትርጉም ባለው መንገድ ለመረዳት ጠቀሜታቸው የጎላ ነበር። ከልዑካኑ መካከል አንዱ ከዩናትድ ኪንግደም ካገኙት እውቀት ውስጥ የገረማቸውን ሲገልጹ “የተዘረጉት ድጋፍ ሰጪ ሥርዓቶች ከምህዳር ጋር ይመሳሰላሉ” ብሏል። ሌላ ልዑክ ደግሞ “የምህዳርን እና የገንዘብ ድጋፍ የማግኘትን አስፈላጊነት” ገልጸዋል። ሌላ ሰው ደግሞ “በዩናትድ ኪንግደም ስላለው የማኅበራዊ ተቋማት ጠንካራ እና ውስብስብ ምህዳር” አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩናትድ ኪንግደምም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ካሉ (ብሪቲሽ ካውንስል፣ ዲኤፍአይዲ [DFID]፣ በእስያ የሥራ ፈጠራ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ከመሳሰሉ) የአመራር አካላት ጋር ለመገናኘት፣ በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በሌሎች አገሮች በዓለም አቀፍ ማኅበራዊ ተቋማትና ተዛማጅ በሆኑ ፕሮግራሞች ላይ ለመወያየት አጋጣሚዎች ለማግኘት አስችሏል። ልዑካኑ ይበልጥ ግንዛቤ ያገኙት የአውሮፓ ሕብረትና ብሪቲሽ ካውንስል በምሥራቅ አፍሪካ እያከናወኑ ስላሉት ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ ለማኅበራዊ ተቋማት መጎልበትና ዘላቂ እድገት ስለለሚሠሩ ዓለም አቀፋዊ ባለ ድርሻ አካላትም ጭምር ነው።

አንድ ልዑክ “ማኅበራዊ ተቋማት ከከፍተኛ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ጋር ብቻ የሚያያዝ ጉዳይ ሳይሆን አቅም ያለውና አዳዲስ ፕሮጀክቶች የሚቀረጹበት ሁኔታ የመፍጠር ጉዳይ ነው።” ጥናታዊ ጉብኝቱ የተጠቃለለው የመጨረሻ የቡድን ሥራ በመሥራት ሲሆን ይህም የጥናቱ ቁልፍ ውጤቶች እንዲዘጋጁ አስችሏል። በዚህ መንገድ የልዑካን ቡድኑ የተገኙትን ትምህርቶች እንዲሁም በኢትዮጵያና በኬንያ ማኅበራዊ ተቋማትን ለማስፋፋት ወደፊት መጓዝ የሚቻልባቸውን የድጋፍ ሐሳቦች አንሸራሽሯል። ከምንም በላይ ደግሞ ልዑካኑ ከሌሎች ተግባሮች በተጨማሪ አማካሪ አካል ለመመሥረት ቁርጠኛ አቋም ይዘዋል፤ ይህም ማኅበራዊ ተቋማትን በልማት ግብ ውስጥ ለማካተት እንዲሁም እድገቱን የሚያጠናክር የደንብ እና የሕግ ድጋፍ ለማዘጋጀት የተጀመረውን ንቅናቄ የሚመራና ወደፊት የሚያስቀጥል ይሆናል። የጥናቱ ውጤቶች፣ በአገራቱ መሥፈርት ለማውጣት በሂደት ላይ ካሉ ጥናቶች ጋር ተዳምረው በባህል ዙሪያ ውይይት እንደማካሄድ ያሉ ቀጣዮቹን እርምጃዎች ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።