Friday 10 February 2017

ማኅበራዊ የሥራ ፈጠራ ተልእኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱት ራሃብ ናይሶቱዋኤ ኬናና፣ የማሳዮችን ጨሌ ለገበያ በማቅረብ በገጠር መንደራቸው ያሉትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ሕይወት የመለወጥ ህልም አላቸው። በኬንያ የሚገኘውን ሰፊ የማሳይ ማራ ክልል የሚጎበኙ ጎብኚዎች ጨሌውን በሚገባ ያውቁታል፤ የራሃብ ህልም ደግሞ ጨሌዎቹን የሚሠሩት ሴቶች ፊታቸው ፈክቶ ወደ ባንክ እንዲሄዱ ማድረግ ነው። ራሃብ እንዲህ ብለዋል፦ "የማሳይ ሴቶች የጨሌ ሥራ በመቶ የሚቆጠሩ አመታትን ያስቆጠረ ባህል ነው፤ ሆኖም ኤኮቱሪዝምን ይበልጥ ለማሳደግ እየጣርን በመሆኑ ይህ ሥራ ለአካባቢው ሕዝብ ጥቅም የሚያስገኝ ጭምር መሆን አለበት።”

በኬንያ የሚገኙ ማኅበራዊ ተቋማትን በሚመለከት በተደረገው ብሪቲሽ ካውንስል ድጋፍ በሚያደርግለት ፎረም ላይ ከተሳተፉት በርካታ ሕዝባዊ እና የግል ሥራ ፈጣሪዎች፣ አጋሮች እና ደንብ አውጪዎች መካከል ራሃብ ይገኙበታል። በትራንስ ማራ ክልል በሚገኙ 15 የማሳይ ሴቶች ቡድኖች ውስጥ የሙያ አማካሪ ሆነው ይሠራሉ፤ ሴቶቹ የጨሌ ሥራቸውን የገንዘብ ማግኛ ምንጭ አድርገው እንዲጠቀሙበት ራሃብ ይረዷቸዋል፦ “የጨሌ ሥራ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የማሳይ ሴቶች ባህል ነው፤ ይሁንና እየተጠቀሙ ያሉት በመሃል ያሉት አሻሻጮች ስለሆኑ የሴቶቱ ሕይወት እየተሻሻለ አይደለም። በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት ሴቶቹ ገበያቸውን ማሳደግ፣ የስርጭት አድማሳቸውን ማስፋት እና የማምረት አቅማቸውን ማሳደግ ይችላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።”

ዩናይትድ ኪንግደም፣ እጅግ ዘመናዊ የሆነ የማኅበራዊ ተቋማት ኤኮሲስተም ካላቸው የዓለማችን አገሮች አንዷ እንደሆነች የታወቀ ከመሆኑም በላይ በዓለም ደረጃ ማኅበራዊ ተቋማት እንዲያድጉ እና ለማኅበራዊ ጉዳዮች መዋእለ ነዋይ ፈሰስ እንዲደረግ ለመደገፍ ቁርጠኝነት እንዳላት አሳይታለች። በናይሮቢው የማኅበራዊ ተቋማት ፎረም ላይ የተገኙት ራሃብ እና ሌሎች ተሳታፊዎች በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ ማኅበራዊ ተቋማት ልምድ እና ከብሪቲሽ ካውንስል የማኅበራዊ ተቋማት አመራር ትምህርት የመቅሰም አጋጣሚ አግኝተዋል። ራሃብ እንዲህ ብለዋል፦ “ከፎረሙ ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ፤ እንዲሁም ናይሮቢ ከመጡ ከሌሎች የማኅበራዊ ተቋማት ቡድኖች ጋር ልምድ ተለዋውጠናል። ይህም ትስስር የምንፈጥርበትን እና በአጋርነት የምንሠራበትን በር ከፍቶልናል። በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ ማኅበራዊ ተቋማት እጅግ ጠቃሚ እውቀት ገብይቻለሁ፤ የማሳይ ቡድኖች አሁን ትኩረት ሰጥተው መሥራት ያለባቸው በአመራር እና በሃላፊነት መዋቅሮቻቸው ላይ መሆን እንዳለበት ተገንዝቤያለሁ።”

በጊዜ ሂደት ቡድኑ ትክክለኛ መዋቅር ኖሮት የጨሌ ሥራው ወደ ማኅበራዊ ተቋምነት ማደግ እንዲችል ለመርዳት የሚውል የ24, 000 የእንግሊዝ ፓውንድ ድጋፍ ከብሪቲሽ ካውንስል አግኝቷል።