Tuesday 24 January 2017

ብሪቲሽ ካውንስል እ. ኤ. አ. ከጥቅምት 2016 ጀምሮ በኢትዮጵያና በኬንያ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የማኅበራዊ ተቋም አመራር ፕሮግራምን የማጎልበትና የማዳረስ ሥራ የሚደግፍ የአቅም ግንባታ እንቅስቃሴ በሰፊው እያከናወነ ይገኛል። ፕሮግራሙ መተግበር በጀመረባቸው የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ወቅት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት የተደረገባቸው የማኅበረሰቡ ክፍሎችና የማኅበራዊ ተቋም አመራሮች፣ በቂ እና ጥራት ያለው የሥልጠና አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ እንዲያገኙና እንዲደርሳቸው ለማድረግ የአቅም ግንባታ አጋጣሚዎችን በመክፈት ረገድ አመርቂ እድገትና ውጤት ተገኝቷል። ከዚህም የተነሳ በተቋም ደረጃ አጋርነት የመመሥረትና የተፈለገውን አቅም ማግኘት ተችሏል። በኢትዮጵያና በኬንያ ከሚገኙ 40 ከሚያህሉ በፕሮጀክቱ ከሚሳተፉ አጋሮች ጋር የሚሠሩ አራት ሲቪል ማኅበራዊ ተቋማት ተመርጠዋል። እነዚህ ተቋማት፣ በሁለቱም አገሮች 1200 ለሚያህሉ የአካባቢያዊና የማኅበራዊ ተቋም አመራር ሰጪዎች ፕሮግራሙን በማጎልበቱና በማዳረሱ ረገድ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል የገንዘብ ድጎማ ተደርጎላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ብሪቲሽ ካውንስል ፕሮግራሙ እንዲጠናከር ለእነዚህ ተቋማት አስፈላጊውን ችሎታና እውቀት ለማስታጠቅ ሲባል ለዋና አሠልጣኞች ብሔራዊ የሥልጠና ዎርክሾፕ አዘጋጅቷል። ከአጋር ተቋሞቹ የተመረጡ በድምሩ 79 የሚያህሉ ዋና አሠልጣኞች አስፈላጊውን ሥልጠና አግኝተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥልጠና የሚሰጡት ዳንየል ስሚዝ እንዲህ ብለዋል፦ “በጥቅሉ ሲታይ ዝግጅቱ ዓላማዎቹን በተሳካ ሁኔታ ዳር አድርሷል ብዬ አምናለሁ። ይህ ገና ጅምር ቢሆንም እንኳን ዎርክሾፑ በኢትዮጵያ ጠንካራ የማኅበራዊ ተቋም ሥነ ምህዳር ለማጎልበት ለተጣለው መሠረት የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።” በሁለቱም አገሮች የሚገኙ ሌሎች አሠልጣኞችና ሠልጣኞችም የእሳቸውን አመለካከት ይጋራሉ ።

ሥልጠናው ጠቃሚ ትምህርት የሚገኝባቸው የተለያዩ ክፍሎችንና ተግባሮችን አካትቶ የያዘ ነበር። ተሳታፊዎቹ በማኅበረሰብ ደረጃ እንዲያዳርሱ ስለሚጠበቅባቸው ማኅበራዊ ተቋምና ፕሮግራም ጥሩ ግንዛቤ አግኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተሳታፊዎቹ የቀሰሟቸው አዳዲስ ተግባራዊ ክህሎቶች በሚገባ ያስታጠቋቸው በመሆናቸው የሥራ ትስስሮችንና ውይይቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማመቻቸት እንዲሁም ፕሮግራሙን ያለ ምንም ችግር ማራመድ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል። ከተሳታፊዎቹ አንዱ ስላገኙት ጥቅም ሲጠየቁ “ያካበትኩት አዲስ እውቀት ለአገራችን በጣም ጠቃሚ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።" አንድ ሌላ ተሳታፊ ደግሞ “ሥልጠናውን ተግባራዊ በማድረግና አብዛኞቹን ዘዴዎች የራሴ በማድረግ ለድርጅቴ እሴት የመጨመር” እቅድ አለኝ ብለዋል። ሥልጠናው በሥራ ፈጠራ የመሰማራት አዲስ መንፈስና ጉጉት እንዲያድርባቸውም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከተሳታፊዎቹ መካከል አንደኛው እንዲህ ብለዋል፦ “ያገኘሁት ሥልጠና ‘ለምን የማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪ ለመሆን አልሞክርም?’ ብዬ ስለ ራሴ እንዳስብ አድርጎኛል።”

ዋና አሠልጣኞቹም ቢሆኑ ትስስሮችንና ግንኙነቶችን ለመመሥረት ነገሮችን የማመቻቸት በቂ ችሎታ እንዳዳበሩ በእርግጠኝነት ተናግረዋል። ተሳታፊዎቹ አሠራሩንና ጥቅሙን በተግባር እንዲያዩት ሲባል ከብሪቲሽ ካውንስል አክቲቭ ሲትዝንስ ዓለም አቀፍ ድረገጽ እንዲሁም ፌስቡክ እና ትዊተር ላይ ከሚገኙ የድርጅቱ የማኅበራዊ ግንኙነት ገጾች ጋር እንዲገናኙ ተደርገዋል። ከኢትዮጵያ የመጣው ቡድን ደግሞ በጉግል ማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ ማኅበራዊ ቡድን መሥርቷል። እንዲህ ዓይነት የአቅም ግንባታ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሳሉ፣ አጋር ተቋሞቹ ሥልጠናውን ለማስቀጠል እቅዶችን በመንደፍና በመተግበር ሂደት ላይ ነበሩ። በዚህ መንገድ የብሪቲሽ ካውንስልን ዲጂታል የመረጃ መለዋወጫ መድረክ በማስፋፋት የግንኙነት ትስስሩም የተሳለጠ እንዲሆን ያደርጋሉ። እንዲህ ያሉ ሂደቱን የሚያፋጥኑ ዘዴዎችና እውቀት ማሰራጫ መስመሮች የሚያስገኟቸው እጥፍ ድርብ ውጤቶች፣ ትልቅ አቅም ላላቸው ታዳሚዎች መጠነ ሰፊ በሆነ እና ዘላቂነት ባለው መልኩ ችሎታ እና እውቀት በማሸጋገር ረገድ ትልቅ ተፅእኖ ያሳድራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመሆኑም ጅምሩ ላይ የተገኘው እድገትና ተስፋ ሰጪ ውጤት፣ ከሌሎች በርካታ ባለ ድርሻ ተቋሞች ጋር በአጋርነትና በመደጋገፍ መተግበር የተጀመረው ፕሮግራምና ተዛማጅ ጥረቶች ገና ከአሁኑ ፍሬ ማስገኘት እንደጀመሩ በግልጽ ያሳያል። እንደ ባጀት የመመደብ ፕሮግራምና ብሔራዊ ሥልጠና የመሳሰሉት አቅም ለመገንባት የተካሄዱት ጅምር እንቅስቃሴዎች፣ የማኅበራዊ ተቋም አመራር እድገት ከፍተኛ እመርታ እንዲያሳይና እጅግ የተፋጠነ እንዲሆን ጠንካራ መሠረት በመጣል ረገድ ወሳኝ ሚና እንደነበራቸው አይካድም።