Crowd of young students cheering

ፕሮግራሙን በተመለከተ

ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን ከለንደኑ የ2012 ኦሎምፒክ በሕግ ጸድቆ የተወረሰ ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙ በብሪቲሽ ካውንስል፣ በዩኒሴፍ እና በዩናይትድ ኪንግደም ስፖርት መካከል የተደረገ የዓለም አቀፍ አጋርነት ውጤት ነው። ፕሮግራሙ የጸደቀው በለንደኑ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችና ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች አዘጋጅ ኮሚቴ (LOGOC) ነው። 

ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ የተደረገው እ. ኤ. አ. ከጥቅምት 2011 እስከ መጋቢት 2014 ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር።

ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን በኢትዮጵያ

የፕሮግራሙ ዓላማ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በርካታ ልጆችና ወጣቶች ከፍተኛ ጥራት ባለውና ዘርፈ ብዙ በሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ስፖርትና በተለያዩ ጨዋታዎች እንዲሳተፉ በመርዳት ጎጂ ባሕላዊ ልማዶችን ጨምሮ አንኳር የሆኑ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የአመራር ብቃትና የሕይወት ክህሎቶች እንዲኖራቸው መርዳት ነው። ፕሮግራሙ በተለይ ትኩረት የሚያደርገው በልጃገረዶችና በአካል ጉዳተኞ ላይ ነው።

ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ያከናወነው ሥራ

ፕሮግራሙን ለማሳካት አብረውን ከሚሠሩ አካላት ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ላቅ ያለ ውጤት ማግኘት ችለናል፦

ብሔራዊው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሥርዓተ ትምህርት ክለሣ

ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን በጉዳዩ ተሳታፊ በመሆኑ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የትምህርት ቤት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሥርዓተ ትምህርት እና የመምህራን ማሠልጠኛ ሥርዓተ ትምህርትን ጥራት ለማሻሻልና መካከት አለባቸው ለተባሉ ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት ሲባል ተከልሷል። 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 21 ሚሊዮን ልጆች ትምህርት ቤት ገብተው ይማራሉ። ከእነዚህ ውስጥ 3 ሚሊዮን የሚያህሉት አንድ ዓይነት የአካል ጉዳት አለባቸው። ስለዚህ ሁኔታው በፖሊሲ ደረጃ ጣልቃ መግባት የሚጠይቅ ሲሆን ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን በአሁኑ ሰዓት በትምህርት ገበታ ላይ በሚገኙ በሁሉም ልጆችና በወጣቶች ላይ እንዲሁም በመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጆች ላይ ጉልህ ለውጥ የማምጣት ሚና እንዲኖረው ተደርጓል።

የኅብረተሰብ የስፖርት ተሳትፎ ብሔራዊ መዋቅር

በኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን ድጋፍ አማካኝነት ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ጋር ተደጋግፎ በቅንጅት በመሥራት የኅብረተሰብ የስፖርት ተሳትፎ ብሔራዊ መዋቅር ሊቋቋም ችሏል። የስፖርት መዋቅሩ ዓላማ ኢትዮጵያ ውስጥ ኅብረተሰቡ ያለውን ደካማ የስፖርት ልምድ መደገፍና ማጠናከር የሚቻልባቸውን አማራጭ ዘዴዎች መቀየስ ነው።

ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በተገኘው አኃዛዊ መረጃ መሠረት በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከአጠቃላዩ ሕዝብ መካከል በስፖርት የሚሳተፈው 0.4% የሚሆነው ብቻ ነው። እጅግ በአብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ በስፖርት የመሳተፍ አጋጣሚ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውን እና የአካል ጉዳተኞች ይህን እድል እንደማያገኙ ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።

ይህን ሁኔታ ለመለወጥና በኢትዮጵያ የኅብረተሰቡን የስፖርት ተሳትፎ ለማሳደግ ብሪቲሽ ካውንስል ከዩናይትድ ኪንግደም ስፖርትና ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት ያሳተፈ የሦስት ቀን ስብሰባ በማድረግ የኅብረተሰብ የስፖርት ተሳትፎ ብሔራዊ መዋቅር አዘጋጅቷል።

የሥራ ሙያ ማሻሻያ ሥልጠና

እስከ አሁን ድረስ ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለ152 የአካል ብቃት ትምህርት መምህራንና በኅብረተሰቡ ውስጥ ላሉ አሰልጣኞች የሥራ ሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ሰጥቷል።

ሥልጠናው የተቀረጸውና የሚሰጠው እጅግ ወሳኝ በሆኑ መስኮች ዙሪያ ሲሆን የሚከተሉትም ይገኙበታል፦

  • የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ልጆችን በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዴት ማሳተፍ እንደሚቻል
  • የአካል ብቃት ትምህርት ማስተማሪያዎችን በአገሪቱ ከሚገኙ ቁሳ ቁሶች እንዴት ማዘጋጀት እንደሚቻል
  • የተማሪዎችን የአካል ብቃት ትምህርት ተሳትፎ እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል
  • በትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ጥራት ያለው የስፖርት ትምህርት እንዴት መስጠት እንደሚቻል
  • በትምህርት ቤቶች ከልጆች ጋር እንዴት መሥራት እንደሚቻል።

ከሥልጠናው በኋላ ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን ትምህርት ቤቶች የአካል ጉዳት በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከመሳተፍ ያግዳል የሚለውን ጠባብ አመለካከት በመዋጋት ረገድ ግንባር ቀደም ሆነው ተገኝተዋል።

School partnership programme

የትምህርት ቤት አጋርነት ፕሮግራም የተመሠረተው በኢትዮጵያና በዩናትድ ኪንግደም የሚገኙ የሁለተኛ ድረጃ ትምህርት ቤቶች ምርጥ ልምዶቻቸውን የሚለዋወጡባቸውን እንዲሁም የየራሳቸውን ባሕል ማድነቅ እንዲችሉ በአስተማሪዎችና በተማሪዎች መካከል ትስስር መፍጠር የሚቻልበት መድረክ ለማቋቋም ነው። በኢትዮጵያ እና በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ በድምሩ ሰላሳ ትምህርት ቤቶች እንዲቆራኙ ተደርጓል።

አጋርነቱ ከተመሠረተ በኋላ በሁለቱም አገሮች የሚገኙ አስተማሪዎች አንዳቸው የሌላውን አገር ጎብኝተዋል። ትምህርት ቤቶቹ እንዲህ ዓይነት ግንኙነት መፍጠራቸው ከአካል ብቃት ትምህርት በዘለለ የትምህርት ቤት የአመራር ብቃት፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋና የሳይንስ ትምህርቶችን ያካተተ ልምድ እንዲለዋወጡ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች በዩናትድ ኪንግደም ካሉ አቻዎቻቸው ጋር ስለ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ልምድ መለዋወጥ የሚያስችላቸው የግንኙነት መስመር ተዘርግቷል።

አጋርነቱ የከፈተውን አጋጣሚ በአግባቡ ለመጠቀም፣ የዩናይትድ ኪንግደም አስተማሪዎች ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ወቅት በማስተማር ዘዴ ዙሪያ የሥልጠና ፕሮግራሞችን አደራጅተው በአጋር ትምህርት ቤቶች የሚገኙ አስተማሪዎች በሙሉ እንዲሳተፉ ተደርጓል።

Youth leadership and life skills training

እስከ አሁን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ 12,472 ልጆችና ወጣቶች በተለያዩ የኢንተርናሽናል ኢንስፓየሬሽን ፕሮግራሞች ሲሳተፉ ቆይተዋል። ከእነዚህ መካከል 1,912 የሚያክሉ ወጣት መሪዎች እንደ ዋይኤስኤል (YSL) እና ቲኦፒኤስ (TOPS) በመሳሰሉ በአመራር ብቃትና በሕይወት ክህሎት ላይ ባተኮሩ ሥልጠናዎች ላይ ተሳትፈዋል።

ከሥልጠናው ዓላማዎች መካከል አንዱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ልጆችና ወጣቶች እንደ ጎጂ ባሕላዊ ልማዶች ያሉ ማኅበራዊ ችግሮችን በመዋጋት ረገድ ተሰሚነት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። በዚህ ሥልጠና ሳቢያ ልጆችና ወጣቶች ጥራት ያለው ትምህርት፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የአካባቢ ጥበቃና ተቻችሎ መኖርን የመሳሰሉ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በማራመድ ረገድ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚችሉ ከትምህርት ቤቶችና ከክልሎች የተገኙ ሪፖርቶች አረጋግጠዋል።

አመራር የሚሰጡት ወጣቶች ከፍተኛ ብቃት ማሳየታቸውን ተከትሎ የፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴርና የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ይህ ሥልጠና በቀጣይነት ለሌሎች 23,400 ልጆችና ወጣቶች እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርበዋል። በአሁኑ ጊዜ ብሪቲሽ ካውንስል ለቀጣይ አሠልጣኞች የአሰልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል። ይህ ሁኔታ ብሪቲሽ ካውንስል ባሠለጠናቸው ልጆችና ወጣቶች አማካኝነት በኢትዮጵያ የወደፊቱን አካሄድ አቅጣጫ በማስያዝ ረገድ ዘላቂ ተጽእኖ ይኖረዋል።

Girls-club training

የኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን ፕሮግራም በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ የልጃገረዶች ክበቦች ሥልጠናዎችን ሰጥቷል።

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 360 ገደማ የሚያህሉ ልጃገረዶች ከዚህ ሥልጠና እየተጠቀሙ ከመሆኑም ሌላ ክበባቸውን በተሳካ ሁኔታ መምራት ችለዋል። በተጨማሪም ክበቦቹ በሴቶች ልጆች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ጉዳዮችን ይኸውም ትምህርት ማቋረጥን፣ ያለ እድሜ ጋብቻንና የቤተሰብ ምጣኔን ለሚመለከቱ ጉዳዮች መፍትሔ በመፈለግ ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው።

Secondary-primary school partnerships

ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን በኢትዮጵያ እያከናወናቸው ካሉት ሥራዎች መካከል አንዱ በአገሪቱ ባሉት የሁለተኛ ደረጃና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል አጋርነትን ማጠናከር ነው።

ይህን ዓላማ ለማሳካት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ የአካል ብቃት ትምህርት መምህራን፣ ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የአካል ብቃት ትምህርት መምህራን የሙያ ማጎልበቻ ሥልጠና በመስጠት ላይ ናቸው። ይህም በአገሪቱ ባሉ ትምህርት ቤቶች ዘላቂና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ሙያ የማጎልበቻ ዝግጅት እንዲጀመር አድርጓል።

College-school partnerships

ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን ኢትዮጵያ፣ በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (በኢትዮጵያ በስፖርት ትምህርት ፕሮግራም ፈር ቀዳጅ የሆነ ተቋም ነው) እና በአካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል አጋርነት የመመሥረት አጋጣሚውን ለማጠናከር ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ጋር በቅርበት እየሠራ ነው።

የዩኒቨርሲቲው የአካል ብቃት ትምህርት ዲፓርትመንት ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን በሚያዘጋጀው የተለያየ ሥልጠና ከተካፈለ በኋላ ዘላቂነት ያለው ሙያን የማጎልበት ሥልጠና ለመስጠት የጥራት ማዕከል ሆኖ በመሥራት ላይ ይገኛል። እስካሁን ድረስ የአካል ብቃት ትምህርት ሴት መምህራን በተለያዩ የሙያ ማጎልበቻ ሥልጠና ክፍለ ጊዜዎች እንዲሳተፉ ተደርጓል።

Netball training

ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን ተግባራዊ በተደረገበት ወቅት ከተለዩት ችግሮች መካከል አንዱ በትምህርት ቤት የሴቶች ልጆች የስፖርት ተሳትፎ አናሳ መሆኑ ነው። ለዚህ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል አንዱ በትምህርት ቤቶች በቂ የጨዋታ ዓይነቶች አለመኖራቸው ነው።

በትምህርት ቤቶች ያለውን የስፖርት ተሳትፎ ለማሳደግ ኢትዮጵያ ውስጥ ለ15 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመረብ ኳስ ሥልጠና እንዲሁም የስፖርት ትጥቆች ተሰጥተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተሳትፎውን ለማሳደግ ሲባል ከዓለም አቀፉ የመረብ ኳስ ማኅበር ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ ለሚገኙ 150 የአካል ብቃት ትምህርት አስተማሪዎችና ከ75 በሚበልጡ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ 200 ሴቶች ልጆች የመረብ ኳስ ሥልጠና ለመስጠት የጋራ ፕሮግራም ተቀርጿል።

ለማኅበራዊ ለውጥ ድጋፍ መስጠት

ኢንተርናሽናል ኢንስፓይሬሽን ታላላቅ ስኬቶችን በመቀዳጀት በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ በሚከተሉት መስኮች ተጽእኖ ማሳደሩን ቀጥሏል፦

  • የሁሉም የትምህርት መስኮች በተለይ ደግሞ የአካል ብቃት ትምህርት ጥራት ጨምሯል።
  • በኢትዮጵያ ሴቶች ልጆችንና የአካል ጉዳተኞችን ጨምሮ የኅብረተሰቡ የስፖርት ተሳትፎ አድጓል።