በAptis መጠቀም የምትፈልጉት እንዴት ነው?

  • ፈተናውን እናንተ ትፈትናላችሁ፦ ፈተናውን በሚያመቻችሁ ሁኔታ እና ጊዜ እናንተ ራሳችሁ መስጠት እንድትችሉ የሚያስፈልጋችሁን ነገር ሁሉ እናሟላላችኋለን። የሚታየውን መሻሻል መቆጣጠር የምትችሉ ከመሆኑም ሌላ የራሳችሁን ሪፖርት ማዘጋጀት ትችላላችሁ።
  • ፈተናውን እኛ እንፈትናለን፦ መሥሪያ ቤታችሁ ወይም ድርጅታችሁ የፈተናውን ሂደት ለመቆጣጠር ጊዜ ሊያጣ እንደሚችል እንረዳለን፤ በመሆኑም ፈተናውን እኛ ልንፈትንላችሁ እንችላለን። ይህም ኮምፒውተሮችን ከማዘጋጀት አንስቶ የፈተና ውጤቶችን እስከ ማደል ይደርሳል። በተጨማሪም ተፈታኞች እንዳያጭበረብሩ እንከታተላለን፤ እንዲሁም ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ፈተናው እንዲካሄድ ቁጥጥር እናደርጋለን።

የፈተና ውጤት

ለእያንዳንዱ የክህሎት ፈተና በደረጃ ውጤት (0-50) የሚሰጥ ሲሆን በዚህ አማካኝነት ዕጩዎችን በግለሰብ ደረጃ ማነጻጸር ይቻላል። ከዚህም ሌላ ተፈታኞቹ ፈተናውን በድጋሚ የሚወስዱ ከሆነ ያሳዩትን መሻሻል ለመለካት ሊረዳችሁም ይችላል።

የፈተናውን ውጤቶች በተናጠል ወይም በአንድ ላይ ለማየት ትመርጡ ይሆናል፤ ይህም በግለሰብም ሆነ በክፍል ደረጃ ሥራቸውን ለመገምገም አጋጣሚ ይሰጣችኋል።

ፈተናው በተለያየ መልክ ሊቀርብ ይችላል

በተለያዩ መንገዶች Aptisን ማቅረብ እንችላለን፦

ኮምፒውተር ላይ የሚሠራ ፈተና

ቀላሉ የ Aptis ፈተና ኮምፒውተር ላይ የሚሠራው ነው፤ ፈተናው፦

  • ለእናንተ አመቺ በሆነው ጊዜ በሥራ ቦታችሁ ላይ ይሰጣል፣
  • በኮምፒውተር ወይም በታብሌት ላይ ይገኛል፣
  • ሰዎች በተለያየ ጊዜ ማለትም ለእነሱ ወይም ለሥራቸው ተስማሚ በሆነ ሰዓት መፈተን ይችላሉ፣
  • አልፎ ተርፎም ተፈታኞች ፈተናውን ከኢንተርኔት ላይ ካወረዱ በኋላ በፈለጉት ሰዓት ኢንተርኔት ሳይጠቀሙ ፈተናውን መሥራት ይችላሉ፣
  • ውጤቱን በቶሎ እንዲያገኙ ያስችላል፣
  • ገንዘብ ቆጣቢ የአቀራረብ ዘዴ ነው።

ወረቀት ላይ የሚሠራ ፈተና

በአንድ ጊዜ ብዙ ተፈታኞችን ለመመዘን በምትፈልጉበት ጊዜ የተለመደውን በወረቀት ላይ የሚሠራውን የፈተና ዓይነት ማግኘት ትችላላችሁ። የመናገር ፈተናውን መፈተን የሚቻለው በኮምፒውተር ወይም በስልክ አማካኝነት ብቻ መሆኑን እባካችሁ አስታውሱ።

ወረቀት ላይ የሚሠራ ፈተና የሚከተሉትን በቀላሉ ማከናወን ያስችላል፦

  • በአንድ ጊዜ ብዙ ተፈታኞችን ለመመዘን፣
  • ኢንተርኔት ወይም ሶፍትዌር መጠቀም ሳያስፈልግ ፈተናውን ለመስጠት፣
  • ተፈታኞች ኮምፒውተር የመጠቀም ችሎታ ባይኖራቸውም እንኳን ችሎታቸውን ለመመዘን።

በስልክ የሚሰጥ ፈተና

የAptis የመናገር ፈተናን በስልክም እንሰጣለን። ይህ የፈተና ዓይነት፦

  • አስቸጋሪ ለሆኑ አካባቢዎች ተስማሚ ነው፣
  • ከሰዓት አንጻር ሲታይ አመቺ ነው፣
  • የኢንተርኔት ግንኙነት እንዲኖር አያስፈልግም፣
  • ‘በዕለት ተዕለት ሕይወት’ የአንድን ሰው ችሎታ ለመፈተን የሚያችል ጥሩ መንገድ ነው፤ በተለይ ሥራችሁ በስልክ የመነጋገርና የመስማት ክህሎትን የሚጠይቅ ከሆነ ይህ ጠቃሚ ነው።

ፈጣን እንዲሁም ገንዘብ ቆጣቢ አሠራርና ውጤት

ከፈተናው ጋር በተያያዘ ያላችሁን ፍላጎት ለማሟላት ከፈተናው በኋላ ባሉት 48 ሰዓታት ውስጥ ውጤት ማሳወቅ እንችላለን። ከዚህ በተጨማሪ የብሪቲሽ ካውንስል ባለሙያዎች የመናገርና የመጻፍ ችሎታን ወዲያውኑ ገምግመው ውጤቱን መስጠት ይችላሉ።

ገንዘብ ቆጣቢ

በዚህ ፈተና አማካኝነት ልትቀጥሯቸው የምትፈልጓቸውን ሰዎች ለመለየት ወይም አሁን ያሉትን ሠራተኞች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ለመመዘን ከፈለጋችሁ Aptis ለሥራችሁ ዘላቂ እሴት የሚጨምር አዋጭ ኢንቨስትመንት ነው።

  • ፈተናው በምትፈልጉት ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲያተኩር በማድረግ መስተካከል ይችላል።
  • የተለያዩ የፈተና ዓይነቶችን አንድ ላይ መውሰድ የዋጋ ቅናሽ እንድታገኙ ሊያደርግ ይችላል።
  • የክፍያው ዝቅተኛ መሆን ሠራተኞቻችሁን በድጋሚ ማስፈተን ያስችላችኋል። በጊዜ ሂደት የችሎታ መሻሻልን ለመመዘን የሚያስችል ግሩም ዘዴ ነው።

 ለሥራችሁ እንዲስማማ ሆኖ ሊስተካከል የሚችል

  • የምትፈልጓቸውን የቋንቋ ክህሎቶች (መጻፍ፣ ማንበብ፣ መናገር ወይም መስማት) መምረጥ ትችላላችሁ ወይም ለተሠማራችሁበት የሥራ ዓይነት ማለትም ለንግድ፣ ለጉዞ፣ ለአስጎብኚነት ወይም ለትምህርት እንዲስማሙ ተደርገው የተዘጋጁትን አራቱንም የፈተና ዓይነቶች መምረጥ ትችላላችሁ።
  • ትኩረት እንዲደረግባቸው በምትፈልጓቸው የሥራችሁ አበይት ጉዳዮች ላይ አነጣጥሩ፦ ተፎካካሪ ሆናችሁ ቀጥሉ እንዲሁም መልካም ስማችሁን ጠብቁ።

ሚዛናዊና አስተማማኝ

Aptis ሁሉም ተፈታኞች ያላቸውን የመጨረሻ የእንግሊዝኛ ችሎታ ማሳየት እንዲችሉ እኩል አጋጣሚ ይሰጣል። ፈተናው የትኛውንም ባሕል እንዳይነካ ታስቦበት የተዘጋጀ ሲሆን ሁሉም ተፈታኞች እኩል የሚስተናገዱበት ከአድልዎ ነፃ የሆነ መድረክ ነው።

የተለያዩ የAptis የፈተና ዓይነቶች ያሉ ሲሆን በየጊዜው አዳዲስ መረጃዎችም ይካተታሉ። ይህም ማለት ተፈታኞች ከጎናቸው ከተቀመጡት ሰዎች ጋር የሚመሳሰሉ ጥያቄዎች አይደርሷቸውም ማለት ነው።

ትክክለኛና እምነት የሚጣልበት ውጤት

የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ በመመዘን ረገድ ከ70 ዓመት በላይ ልምድ አለን።

በ Aptis የሚሰጠው ውጤት ትክክለኛ እና እምነት የሚጣልበት ነው፦ በሙያው የተካኑ ፈታኞቻችን የመጻፍ እና የመናገር ፈተና ውጤቶችን በሚያርሙበት ጊዜ በተደጋጋሚ ፈተና የወሰዱ ተፈታኞች ተመሳሳይ ውጤት እንደሚያገኙ ጥናቶች አሳይተዋል። የቋንቋ ችሎታ ለመፈተን ስለምናደርገው ሳይንሳዊ ጥናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የምርምር ውጤቱን የምናወጣበትን ገፅ ይጎብኙ።

ያገኛችሁት ውጤት ደረጃ የሚወጣለት በ ኮመን ዩሮፒያን ፍሬምወርክ ኦፍ ሬፈረንስ ፎር ላንጉዌጅስ (CEFR) መሠረት ነው። ፈተናው ለእያንዳንዱ የክህሎት ፈተና (A1-C) አጠቃላይ የCEFR ደረጃ ይሰጣል። በአራቱ የክህሎት ዘርፎች ሁሉንም ፈተናዎች ከወሰዱ አጠቃላዩን የCEFR ደረጃ የሚያንጸባርቅ ውጤት ያገኛሉ። CEFR በመላው ዓለም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታን ብቃት ለመለካት እንደ መዋቅር ሆኖ ይሠራበታል።