Connecting Classrooms ©

Credit Matt Wright

ፎቶ፦ ማት ራይት

የፕሮግራሙ ዓላማ

የዓለማችን ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ሥነ ምህዳራዊ ሁኔታ አለማቋረጥ እየተለወጠ በመሆኑ ወጣት ዜጎች በዚህ ዓለም ላይ ያላቸውን ድርሻ ማወቃቸው ወሳኝ ነገር ነው።

ኮኔክቲንግ ክላስሩምስ የሚባለው ትምህርት ቤቶችን ታሳቢ በማድረግ የቀረጽነው ዓለም አቀፍ የትምህርት ፕሮግራም አስተማሪዎች ከላይ የተጠቀሰውን ግብ ማሳካት እንዲችሉ ለመርዳት የተዘጋጀ ነው።

እንደ አንድ መንደር በሆነው ማህበረሰብ ውስጥ ሁሉም ወጣቶች ስኬታማ መሆን እንዲችሉ አጋጣሚውን የመክፈት ዓላማ አለን። ኮኔክቲንግ ክላስሩምስ ፕሮግራም ተማሪዎችንም ሆነ አስተማሪዎቻቸውን በሚከተሉት መስኮች ብቁ ያደርጋል:-

  • በዓለም አቀፍ ደረጃ አንገብጋቢ የሆኑ ጉዳዮችን እንዲገነዘቡ ማስቻል፣
  • በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲገነዘቡ ማድረግ፣
  • ዓለም አቀፍ በሆነው ኢኮኖሚ ስኬታማ እንዲሆኑ የሚረዷቸውን ክህሎቶች እንዲያዳብሩ መርዳት።

ኮኔክቲንግ ክላስሩምስ ፕሮግራምን ከጀመርንበት ከ2006 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ በዩናይትድ ኪንግደምና በኢትዮጵያ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል ለተመሠረቱ ከ50 በላይ የሚሆኑ ትስስሮች ድጋፍ ስንሰጥ ቆይተናል፣ ከ2000 ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን አስተማሪዎች የተለያዩ ኮርሶችንና የኢንተርኔት ስልጠናዎችን ሰጥተናል እንዲሁም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ከ1000 በላይ የሚሆኑ ርዕሰ መምህራን የአመራር ብቃታቸውን እንዲያጎለብቱ ረድተናል።

መማሪያ ክፍሎችን የምናስተሳስረው እንዴት ነው?

መማሪያ ክፍሎች የሚተሳሰሩባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፤ ከእነዚህም መካከል አብሮ መስራት፣ በኢንተርኔት ልምድ መለዋወጥ፣ መምህራን አጋር ትምህርት ቤቶችን እንዲጎበኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ ሙያን ማጎልበት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር እና ዓለም አቀፍ የትምህርት ቤት ሽልማት (International School Award [ISA]) ይገኙበታል።

አጋር መሆን

እርስዎ የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት በውጭ አገር ከሚገኝ ትምህርት ቤት ጋር አብሮ ይሠራል? ከሆነ ከኮኔክቲንግ ክላስሩምስ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ይቻላል። በፕሮግራሙ መታቀፍዎ በእርስዎ ስር ያሉ ልጆችን የዓለም አቀፍ ዜጋ አድርጎ ኮትኩቶ ለማሳደግና በመምህርነት ሙያዎት እድገት ማድረግ እንዲችሉ ይረዳዎታል፤ እንዲሁም በሌሎች አገሮች ከሚገኙ የሥራ ባልደረቦችዎ ጋር መልካም ተሞክሮዎችን በመጋራት ተጠቃሚ ይሆናሉ።

እርስዎም የዚህ ግሩም ፕሮጀክት አባል መሆን ይችላሉ።

በአባልነት መታቀፍ ቀላል ከመሆኑም በላይ ምንም ክፍያ አይጠየቁም፤ እኛም ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ርዕሰ ጉዳዮች በትምህርት ቤቱ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተቱ እንዲሁም ዘላቂ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት እንዲመሰርቱ ልንረዳዎት እንችላለን።

በተጨማሪም በፕሮግራሙ የታቀፉ ትምህርት ቤቶችን መጎብኘት እንዲችሉ እና ለፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ እናደርጋለን።

የፕሮግራሙ አባል ለመሆን አሊያም የበለጠ መረጃ ለማግኘት ብሪቲሽ ካውንስል ትምህርት ቤቶች የኢንተርኔት ድረገጽን ይመልከቱ ወይም ቀጥሎ በተገለፀው አድራሻ ይፃፉልን፦ information@et.britishcouncil.org.

 ኮንቲኒዊንግ ፕሮፌሽናል ዴቨሎፕመንት (CPD)

አባል ትምህርት ቤቶች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመርዳት ስንል የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን የምናዘጋጅ ከመሆኑም ሌላ በኢንተርኔት ኮርሶች እንሰጣለን።

በኢንተርኔት የምንሰጣቸው ኮርሶች ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጉዳዮች በሚመለከት መረጃና ምክር ይሰጣሉ፦

  •  የመሰረታዊ ክህሎቶች ስልጠና፣
  • የባህል ልዩነቶችና ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ፣
  • ስኬታማ የሆነ ዘላቂ አጋርነት፣
  • የተለያዩ የሥራ ሙያ ማዳበሪያዎች፦ አጠቃላይ ስልጠና፣ የሕጻናት ጥበቃ፣ የትምህርት ቤት አስተዳደር፣ ወዘተ . . .
  • የመረጃና የግንኙነት ቴክኖሎጂ (ICT) ለዓለም አቀፋዊ ትብብር ስላለው ጥቅም፣
  • እንግሊዝኛ ለዓለም አቀፋዊ የንግድ ልውውጥ፣

ከእነዚህ ኮርሶች መካከል አንዱን ለመውሰድ ለመመዝገብና ስልጠናውን ለመጀመር ኮኔክቲንግ ክላስሩምስ መማሪያ ድረገጽን ይጎብኙ።

ከዚህ በተጨማሪ በተለይ ለኢትዮጵያውያን መምህራን በተዘጋጁ መሰረታዊ ክህሎቶች የሚያስገኙ ስልጠናዎች ላይ በአካል ተገኝተው መሳተፍ ይችላሉ። ፕሮግራሙ የመጀመሪያ ደረጃና ከፍተኛ ደረጃ ተብሎ የተከፈለ ሲሆን የተዘጋጀው፦

  • ያካበቱትን ልምድና እውቀት ማካፈል እንዲችሉ፣
  • ስለ ዓለም አቀፋዊ ዜግነት ያለዎት እውቀት መሠረታዊ ወይም መጠነ ሰፊ ቢሆንም እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ልምድ ያካበቱ ቢሆኑም ባይሆኑም ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣
  • የሥራ ተነሳሽነትን በአዲስ መልክ ለማነቃቃት፣
  • በትምህርት ቤት ሊተገብሯቸው የሚችሏቸውን አዳዲስ ሃሳቦች ለማመንጨት፣
  • የትምህርት ቤታችሁ ሥርዓተ ትምህርት ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ለማበረታታትና ለማስታጠቅ ነው።

የትምህርት ቤት አመራር አካላት በትምህርት ቤታቸው ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው የትምህርት አሰጣጥ እንዲተገብሩ የሚረዳ ሌላም ስልጠና እንሰጣለን። ይህ የስልጠና ፕሮግራም 20 ክፍሎች ያሉት ሲሆን ለአካባቢው እንደሚመች ተደርጎ መስተካከል የሚችል ነው። በዚህ ስልጠና ላይ መካፈል የሚፈልጉ ከሆነ ቀጥሎ በተገለጸው አድራሻ ይጻፉልን፦ information@et.britishcouncil.org.

 ዓለም አቅፍ የትምህርት ቤት ሽልማት (International School Award)

ከአጋር ትምህርት ቤቶች ጋር ለመሥራት ብርቱ ትጋት ላሳዩ ወይም ለዓለም አቀፋዊ ባህሎችና ጉዳዮች ፍላጎት እንዲያድርባቸው በማድረግ የተማሪዎቻቸውን ሕይወት በዘላቂነት እያሻሻሉ ላሉ ትምህርት ቤቶች ዓለም አቀፍ የትምህርት ቤት ሽልማት [International School Award (ISA)] በመሸለም እውቅና እንሰጣለን።

[ዓለም አቀፍ የትምህርት ቤት ሽልማት፣ በአንድ አገር በተዋቀረበት መንገድ ላይ ተመሥርቶ እንደ አማራጭ የቀረበ ሃሳብ፦ ለሁሉም ትምህርት ቤቶች በነፃ የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ ድጋፍ የሚሰጥባቸው ሦስት ደረጃዎች (የመጀመሪያ፣ መካከለኛ፣ ሙሉ) አሉ።

ስለ ዓለም አቀፍ የትምህርት ቤት ሽልማት [International School Award (ISA)] ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እንዲሁም እርስዎም በፕሮግራሙ እንዴት መካተት እንደሚችሉ ለማወቅ ብሪቲሽ ካውንስል ትምህርት ቤቶች የኢንተርኔት ድረገጽን ይጎብኙ።

 ስለ ፖሊሲ የሚካሄድ ውይይት

ከትምህርት ፖሊሲ አውጪዎች ጋር አብረን በመሥራት ግንኙነትና ትስስር የምንፈጥር ከመሆኑም ሌላ በትምህርት አሰጣጥ እና በዓለም አቀፋዊ ዜግነት ረገድ የተሻለ አማራጭ እንዲጠቀሙ እናበረታታቸዋለን፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ብሄራዊ ጉዳዮች ድጋፍ እናደርጋለን።

ተሳታፊ አገሮችን የሚጎበኙበት ፕሮግራም የምናዘጋጅ ሲሆን በዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች ላይ የተለያዩ አጀንዳዎችን እንዲያነሱና የሃሳብ ልውውጥ እንዲያደርጉ እናበረታታዎታለን። የበለጠ መረጃ ለማግኘት ቀጥሎ በተገለፀው አድራሻ ይፃፉልን፦ information@et.britishcouncil.org.

 ተጨማሪ መረጃ

ስለ ኮኔክቲንግ ክላስሩምስ ፕሮግራም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እንዲሁም እርስዎም በፕሮግራሙ እንዴት መካተት እንደሚችሉ ለማወቅ ኮኔክቲንግ ክላስሩምስ ድረገጽን ይጎብኙ።