ብሪቲሽ ካውንስል በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ላሉ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ መስጠት ጀምሯል። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 52,000 ስደተኞች ያሉባቸው አራት መጠለያዎች አሉ። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) እ. ኤ. አ. እስከ 2016 አጋማሽ ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ 850, 000 ገደማ ስደተኞችን እንደተቀበለች ይፋ አድርጓል፤ ይህ ከአፍሪካ ከፍተኛው ቁጥር ሲሆን ከዓለም ደግሞ አምስተኛው ነው። ብሪቲሽ ካውንስል በቦታው ያለውን የቋንቋ ፍላጎት ለማወቅ እ. ኤ. አ. የካቲት 2016 ላይ የተወሰነ ጥናት አካሂዶ የነበረ ሲሆን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙት የስደተኛ መጠለያዎች ውስጥ ከ30 በላይ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች እንደሚነገሩና የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ሆኖ የሚያገለግለው እንግሊዝኛ እንደሆነ ማወቅ ተችሏል።
በተጨማሪም ስደተኞች በሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ለውጥ በሚያመጡ ፈተናዎች የተማሪዎች ውጤት በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከሚያመጡት ውጤት በጣም ያነሰ ነው። በኢትዮጵያ ከሚገኙ የአንደኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በተለየ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርቱ የሚሰጠው በእንግሊዝኛ ነው። ከዩኤንኤችሲአር እና ከስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ አስተዳደር (ARRA) ጋር በርካታ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ብሪቲሽ ካውንስል ስደተኞቹ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለማቃለል ሲል ይህን የሙከራ ፕሮጀክት ጀምሯል።
የዚህ የሙከራ ፕሮጀክት ዓላማ፣ በተመረጡት አራት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰጡትን ትምህርቶች ጥራት ለማሻሻልና የአስተማሪዎቹን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ለማሳደግ ነው። ከሁሉም ትምህርት ቤቶች መነሻ የሚሆን መረጃ የሰበሰብን ከመሆኑም ሌላ ከአራቱ ትምህርት ቤቶች የአስተማሪዎች አሠልጣኞች የሚሆኑ አስተማሪዎችን መርጠናል። እነዚህ የአስተማሪዎች አሠልጣኞች በመጀመሪያ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ እነሱ በመጡባቸው ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ ሌሎች አስተማሪዎች ሥልጠና ይሰጣሉ።
የሙከራ ፕሮግራሙ ጠንካራ ክትትልና ግምገማ የሚደረግለት ከመሆኑም ሌላ የትምህርት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶለታል። የውጭ አማካሪዎችና የብሪቲሽ ካውንስል ሠራተኞች ለአስተማሪዎቹ ድጋፍና ክትትል እያደረጉላቸው ነው። ይህ የሙከራ ፕሮግራም ስኬታማ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ሌሎች አራት የስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ ፕሮጀክቱ ሊስፋፋ ይችላል።