'The vision is to create world-class universities, based on African models and solutions.' ©

Mat Wright.

የአፍሪካ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ ነው፤ የብሪቲሽ ካውንስል ባልደረባ የሆኑት ካሮሊን ቺፐርፊልድ እንደገለጹት በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲዎች የሚጫወቱትን ሚና መገንዘብ ይኖርብናል። አፍሪካ ግቦቿን ለማሳካት ለከፍተኛ ትምህርት ቁልፍ ቦታ ትሰጣለች።

አጀንዳ 2063 54ቱ የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት አፍሪካን ለመቀየር እ. ኤ. አ. በ2013 የተስማሙበት ዕቅድ ነው። አጀንዳ 2063 ‘በጋራ እሴቶችና ግቦች ላይ የተመሠረተች የበለጸገች እና አንድነት ያላት አፍሪካን ለመገንባት’ የ50 ዓመት ዕቅድ አውጥቷል። ዕቅዱ የአፍሪካን ‘ሕዳሴ’ የሚያራምድ ሲሆን፣ ይህ መንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ ለትምህርት፣ ለቴክኖሎጂ፣ ለሳይንስና ለምርምር በሚያፈስሰው መዋዕለ ነዋይ ላይ የተመካ ነው።

አፍሪካ እ. ኤ. አ. ለ2063 ያላት ራእይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ተማሪዎች መካከል ቢያንስ 70 በመቶ የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲ እና የኮሌጅ ትምህርት እንዲቀጥሉ ማስቻል ነው፤ ከሚመረቁት መካከል ደግሞ 70 ከመቶ የሚሆኑት ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዙ ትምህርቶች እንዲሆን ይፈለጋል። ይህን በንጽጽር ለማየት አሕጉሪቱ ያወጣችው ግብ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በአማካይ 32 በመቶ ከሆነው የተመዝጋቢዎች ቁጥር በእጥፍ የሚበልጥ ሲሆን አሁን ከሰሐራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች አማካይ ከሆነው ስምንት በመቶ በስምንት እጥፍ ይበልጣል። ይህን ተግዳሮት በመወጣት፣ እንዲሁም በመላ አሕጉሪቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ እ. ኤ. አ. በ2063 በአፍሪካ የተመዝጋቢዎች ቁጥር በዩናይትድ ኪንግደም ከነበረውየ2013 የተመዝጋቢዎች ቁጥር (በወቅቱ 60 በመቶ ነበር) ጋር ተቀራራቢ ያደርገዋል።

ይህ ከፍተኛ ተነሳሽነት ፍሬ ማፍራት ጀምሯል። በመላው አፍሪካ መንግሥታት ከፍተኛ ትምህርት ከስኬት ተነጥሎ እንደማይታይ ቆጥረውታል፤ ግለሰቦች ደግሞ ጥሩ ገቢ ለማግኘትና ይበልጥ አርኪ የሆነ ሥራ ለመያዝ እንደሚያስችል ያምናሉ። ይህም በመላ አሕጉሪቱ ከፍተኛ ትምህርት በፍጥነት እንዲስፋፋ በማስቻሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ አስችሏል።የዩኔስኮ የስታትስቲክስ መረጃ ተቋምበገለጸው መሠረት በአፍሪካ ለዩኒቨርስቲ እና ለኮሌጅ ትምህርት የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር በለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በእጥፍ ጨምሮ ከስድስት ሚሊዮን ተነስቶ ከ12 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

ቁጥሩ በእጅጉ እየጨመረ የመጣው ወጣት ትውልድ በአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ፍላጎት እንዲጨምር አድርጓል።

በቅርቡ የተዘጋጀየዓለም ባንክ ሪፖርትእንደሚያሳየው ከሰሐራ በታች የሚኖሩ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች በቀጣዩ አሥር ዓመት ውስጥ በየዓመቱ የሥራውን ዓለም ይቀላቀላሉ። የወጣቶቹ ቁጥር ለቀጣዮቹ 60 ዓመታትም በከፍተኛ መጠን ማደጉን እንደሚቀጥልና በአፍሪካ ያሉ ወጣቶች ቁጥር በእስያ ካሉ ወጣቶች ቁጥር ጋር እኩል እንደሚሆን ከዚያም እ. ኤ. አ. በ2078 ገደማ በልጦ እንደሚሄድተገምቷል።

ይህ ለኢኮኖሚው መልካም ዜና እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። የአፍሪካ አጠቃላይ አገራዊ ምርት (GDP) እ. ኤ. አ. በ2015 ጥንካሬው ጨምሮ በ4.5 በመቶ፣ እ. ኤ. አ. በ2016 ደግሞ በ5 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል፤ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገው ነገር ስለ ኢኮኖሚው ያለው እውቀት ማደግና አዳዲስ የተማረ የሰው ኃይል ወደ ሥራው ዓለም መቀላቀሉ ነው።

ምሥራቅ አፍሪካ ይህን የመማር ፍላጎት በማሟላት ረገድ ፈጣን ምላሽ ሰጥታለች

በምሥራቅ አፍሪካ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ጨምሯል። መንግሥታት ለምርምርና ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት እየሰጡ ናቸው፤ ይህም የሆነው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ሰጪ ኢኮኖሚ መሸጋገር ለኢኮኖሚ እድገት እንደሚጠቅም በመገንዘባቸው ነው። ይህ ለውጥ የተለያዩ ሙያዎች እና አዳዲስ እውቀቶች እንዲያስፈልጉ ምክንያት ሆኗል።

ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት አስደናቂ ለውጥ በማድረግ ረገድ ተጠቃሽ አገር ናት፤ በአሁኑ ጊዜ ‘የአፍሪካ ነብሮች’ ተብለው በሰፊው ከሚታወቁ አገሮች አንዷ ስትሆን እ. ኤ. አ. በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ሰፊ ዕቅድ አላት። በክልሉ እንዳሉ በርካታ አገሮች ሁሉ ኢትዮጵያም ግቦቿን ለማሳካት እንዲሁም ዜጎቿንና ተቋሞቿን ለማሳደግ ከፍተኛ ትምህርት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ትገነዘባለች። ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ቁጥር በ40 በመቶ ጨምሯል፤ ባለፉት 20 ዓመታት ደግሞ 60 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች (ግማሾቹ የግል ናቸው) ተከፍተዋል። የዩኒቨርስቲ እና የኮሌጅ ትምህርት መከታተል በሚችሉበት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ3.6 ሚሊዮን ወደ 13 ሚሊዮን በማደጉ፣ በአገሪቱ ያለው የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓት እ. ኤ. አ. እስከ 2025 ባሉት ቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ 1.7 ሚሊዮን የሚያህሉ ተጨማሪ ተማሪዎች በተለያዩ ፕሮግራሞች እንዲታቀፉ ያደርጋል።

ምሥራቅ አፍሪካ ከከፍተኛ ትምህርት ጋር የተያያዙ ሌሎች ብዙ ተግዳሮቶች ተደቅነውባታል

በምሥራቅ አፍሪካ የታየው አስደናቂ የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት አልጋ በአልጋ የነበረ አይደለም፤ እዚህ ላይ ምሥራቅ አፍሪካ ስንል አሥር አገሮችን ይኸውም ታንዛኒያን፣ ቡሩንዲን፣ ሩዋንዳን፣ ዩጋንዳን፣ ሱዳንን፣ ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን፣ ጂቡቲን፣ ሶማሊያን እና ኬንያን ማለታችን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በመላ አሕጉሪቱ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከፍተኛ የአስተማሪዎች እጥረት አለ። የዩኒቨርስቲ አስተማሪ ለመሆን የሚፈልግ ሰው የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪውን ትምህርት እና ሥልጠና ለማጠናቀቅ አሥር ዓመት ገደማ ይወስድበታል። ይህ ሁኔታ የዩኒቨርሲቲ ዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው የዩኒቨርስቲ አስተማሪዎች ቁጥር በመቶኛ ሲታይ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ እ. ኤ. አ. በ2013/14 በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ውስጥ ካሉ አስተማሪዎች ውስጥ ለፒኤችዲ ደረጃ የበቁት 11 ከመቶ ብቻ ነበሩ። ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች፣ ከዓለም አቀፉ አማካይ ቁጥር አንጻር ሲታይ እያንዳንዱ የዩኒቨርስቲ አስተማሪ50 በመቶ ተጨማሪ ተማሪዎች ይኖሩታል፤ ከዚህም ሌላ እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት አዳዲስ የዩኒቨርስቲ አስተማሪዎች ከየት ሊመጡ እንደሚችሉ የሚታወቅ ነገር የለም። መማሪያ ክፍል ውስጥ ብዙ ተማሪዎች መኖራቸው እና አስተማሪዎች ጫና ያለባቸው መሆኑ ተማሪዎች የሚቀስሙት ልምድ ጥራት እንዲጎድለው የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዘርፍ ለማቋቋም እንዲቸገር ያደርጋል። በዚህ ረገድ አስተማሪዎችን የመመልመሉ፣ የማሠልጠኑና በሥራቸው እንዲቀጥሉ የማድረጉ ጉዳይ አንገብጋቢ ይሆናል።

በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ የሚመረቁ ተማሪዎች ቁጥር መጨመሩ አሠሪዎች የጥራት ደረጃን በተመለከተ አንድ የተለመደ ቅሬታ እንዲያሰሙ አድርጓቸዋል፦ ተመራቂዎቹ የተማሩ ሊሆኑ ቢችሉም በቀጥታ ለሥራው የሚያስፈልግ እውቀትናክህሎት ይጎድላቸዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት የወደፊት ተስፋው ምንድን ነው?

ከእነዚህ ጫናዎች ጋር በተያያዘ በርካታ አጋጣሚዎች የሚከፈቱ ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ትምህርት በተለያዩ መስኮች የተለያዩ ፍላጎቶችን በተሻለ ሁኔታ ማሟላት እንዲችል ቅርጽ መስጠት የሚቻልበት እድል ይኖራል። ለምሳሌ ያህል፣ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ትስስር በመፍጠርበአካባቢው ያሉ ችግሮችን መፍታት የሚቻልበት አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። ይህ በክልሎች መካከል በሚዘጋጁ የጉብኝት ፕሮግራሞች አማካኝነት ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ግንኙነት እንዲኖራቸው በማድረግ በአገሮች መካከል የእውቀት ሽግግር የሚፈጠርበት አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። የተለያየ ኑሮና አስተዳደግ ያላቸው ተማሪዎች ከፍተኛ ትምህርት የመማር አጋጣሚ የሚያገኙበትም ሊሆን ይችላል።

በአጭሩ፣ ራእዩ ኅብረተሰቦችና ብሔራት እንዲለወጡ እንዲሁም የዛሬንም ሆነ የነገን አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች እንዲወጡ ሊረዱ የሚችሉ አፍሪካዊ በሆኑ ዘዴዎች እና መፍትሔዎች ላይ የተመሠረቱ ዓለም አቀፋዊ ደረጃቸውን የጠበቁ ዩኒቨርሲቲዎች መፍጠር ነው።’

ጎይንግ ግሎባል የተሰኘው የከፍተኛ ትምህርት አመራሮች ዓለም አቀፋዊ ዓመታዊ ስብሰባ እ. ኤ. አ. በ2016 በደቡብ አፍሪካ ይካሄዳል። እ. ኤ. አ. ከጥር 25 ቀን 2016 ጀምሮ መመዝገብ ይቻላል። የስብሰባው ጭብጥ ‘ብሔራትን መገንባትና ባሕሎችን ማስተሳሰር፦ ትምህርት፣ ፖሊሲ፣ የኢኮኖሚ እድገትና ተሳትፎ’ የሚል ነው።

ኢራስመስ + ባዘጋጀውኢንተርናሽናል ክሬዲት ሞቢሊቲ በተባለው ፕሮግራም አማካኝነት በአውሮፓ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ከአውሮፓ ውጪ ካሉ በርካታ አጋር አገሮች ጋር የተማሪዎችና የአስተማሪዎች የልምድ ልውውጥ ማድረግ ይችላሉ። እ. ኤ. አ.በ2016 ኢትዮጵያንና ሩዋንዳን ጨምሮ በአፍሪካ፣ በካሪቢያን እና በፓሲፊክ ክልሎች የሚገኙ ሌሎች አገሮች በፕሮግራሙ ታቅፈዋል።

ውጫዊ ማያዣዣዎች