ማኅበራዊ ተቋሞች ምንድን ናቸው?

 ማኅበራዊ ተቋሞች በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ችግሮችን የሚፈቱ ድርጅቶች ናቸው። እንደ ሌሎች የንግድ ሥራዎች ሁሉ የሥራ እድል ይፈጥራሉ እንዲሁም ገቢ ያስገኛሉ፤ ይሁንና የተገኘው ትርፍ ለባለቤቶቹ ጥቅም ከማስገኘት ይልቅ ማኅበራዊ ተልእኳቸውን ለመደገፍ እና ለማጠናከር ላይ ይውላል። በዚህ መንገድ ተቋሞቹ በኅብረተሰባችን ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሕይወት እንዲሻሻል ያደርጋሉ።

የምናከናውነው ሥራ

በዚህም መሰረት የማኅበራዊ ተቋም ሥራዎችን ለማከናወን በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች ከበርካታ ባለ ድርሻ አካላት ጋር አብረን እንሠራለን።

ፖሊሲ አውጪዎችና ተፅእኖ ፈጣሪዎች

በዚህ ፖሊሲ ተኮር ሥራ አማካኝነት የመንግሥትና ቁልፍ የሆኑ የፖሊሲ አውጪ አካላት አቅም እንዲጎለብት በመርዳት ለማኅበራዊ ተቋማት የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸውን ድጋፍ እንሰጣለን። ይህ ደግሞ ተግባራዊ ለማድረግየሚያስችል አቅጣጫ መቀየስን፣ በአውሮፓ ሕብረት አገሮች የሚደረጉ ትምህርታዊ ጉብኝቶችን መምራትን እንዲሁም ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት መሠራት ያለባቸውን ነገሮች በጋራ መወሰን እንዲችሉ በፖሊሲ ዙሪያ ለመነጋገር መሰብሰብን ይጨምራል።

የማኅበራዊ ተቋማት ድጋፍ ሰጪዎች

የዘርፉን አቅም ለመገንባት የምናከናውነው ሥራ ድጋፍ ሰጪ የሆኑ ድርጅቶችን ይኸውም የአደራጆችን፣ የአሰልጣኞችን፣ የአማካሪዎችን እንዲሁም የኢንቨስትመትና የፋይናንስ ባለ ሙያዎችን አቅም በመገንባት ላይ ያተኩራል። ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችና አሰልጣኞችለማኅበራዊ ተቋማት አመራሮች የተሻለ የሥራ ድጋፍ እንዲሰጡ እርዳታ እናደርጋለን። የማኅበራዊ ተቋማት አደራጆች የሚሰጣቸው ከፊል ድጎማ ሲሆን ይህም መመሪያ እና ሥልጠና መስጠትን እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ከሚመለከታቸው የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ጋር የመልካም ልምዶች ልውውጥ ማድረግን ይጨምራል።

የማኅበራዊ ተቋም ተሳታፊዎች

በተጨማሪም በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ የማኅበራዊ ተቋም ማኅበረሰቦች እንዲያድጉ የሚያስችላቸውን ድጋፍ እንሰጣለን፤ ይህን የምናደርገው የማኅበራዊ ተቋምና የሲቪል ማኅበራዊ ድርጅት አመራሮች ግንኙነትና ትስስር መመሥረት እንዲችሉ እንዲሁም በጋራ መሥራትና አጋርነት መፍጠር የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች በመስጠት ነው። ማኅበራዊ ተቋሞች በጠቅላላው የምሥራቅ አፍሪካ ክልል በሙሉ በሚገኙ የማኅበራዊ ተቋም ተሳታፊዎች መካከል በሚፈጠር ትስስር አማካኝነት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሚገባ መግለጽና ልምድ መለዋወጥ የሚችሉበትን አቅም ለመገንባት መድረክ እናመቻቻለን፤ እንዲሁም ከአቻ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ጋር ተሞክሮ የሚለዋወጡበትን ሁኔታ እናመቻቻለን።

የምንጠቀምበት ዘዴ

ሁሉን አሳታፊ የአሠራር ዘዴ

ከመላው የማኅበራዊ ተቋም ዘርፍ የተገኘውን እውቀትና አመለካከት ለመጋራት ከማኅበራዊ ተቋም ተሳታፊዎች፣ ድጋፍ ሰጪ አካላትና ደንብ አውጪዎች ጋር እንሠራለን፤ ይህ ግልፅ በሆነና ሥርዓት ባለው መንገድ ለሚሰጥ ምላሽ ድጋፍ እንድናደርግ ያስችለናል።

ተደጋግፎ የመሥራት ዘዴ

ተደጋግፎ የመሥራት መርህ የሥራችን ሁሉ መሰረት ነው። በጋራ የምናሳድረውን ተጽእኖ በተቻለ መጠን ለማጠናከር እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካና በአውሮፓ ባሉ ተደጋግፈው የሚሠሩ አገሮች መካከል ትስስር ለመፍጠር ከበርካታ ተሳታፊዎች ጋር አጋር ሆነንና ተደጋግፈን እንሠራለን።

አስፈላጊነቱ

የምናከናውናቸውን ሥራዎች ካሉት አጀንዳዎችና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር የማያያዝ ፍላጎት አለን። ማኅበራዊ ተቋሞች በአንድ አገር ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ሁኔታዎች መፍትሔ እየሰጡ በሄዱ መጠን ይህ ዘርፍ መጠነ ሰፊ ለሆነ አገራዊ የለውጥ አጀንዳ፣ የእድገት እቅድ ወይም ዘላቂ የእድገት ግቦች መፍትሔ ሆኖ እንዲታይና ግንኙነት እንዲኖረው እናደርጋለን።

በማስረጃ የተደገፈ

በመስክ ላይ የተፈተኑ የአሠራር ዘዴዎችን ለማጎልበትና ለማሳየት የሙከራ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ በማስረጃ ላይ የተደገፈ የማኅበራዊ ተቋሞች አሠራር ለማበረታታትና ለማጠናከር የሚረዳ ጠንካራ የሆነ መረጃ እናዘጋጃለን።

በኢትዮጵያ ያለን ፕሮግራም

ኢትዮጵያ በመስኩ ተሳትፎ ማድረግ የጀመርነው ጥናታዊ ሥራ በማከናወን ሲሆን በጥናቱ አማካኝነት በአገሪቱ ስላለው የማኅበራዊ ተቋሞች ወቅታዊ ሁኔታ ለማወቅ ጥረት ተደርጓል። ጥናቱ በአገሪቱ ዘርፉ የሚገኝበትን አጠቃላይ ገጽታ ያሳየ ከመሆኑም በተጨማሪ የማኅበራዊ ተቋሞችን መጠንና ሁኔታ መገምገምን ያካተተ ነበር። ይህ ደግሞ በበኩሉ የሥነ ምህዳሩ ቁልፍ ተሳታፊዎች የሚወያዩበት መድረክ ለመክፈትና ለማኅበራዊ ተቋሞች የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር ይረዳል።

አቅመ ደካማ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተደቀኑባቸውን ተግዳሮቶች በመወጣት ረገድ ለማኅበራዊ ተቋሞች ድጋፍ መስጠት የሚያመጣውን ለውጥ ለማሳየት ፕሮግራሙ ለማኅበራዊ ተቋም ድጋፍ የሚሰጡ እንደ ሲቪል ማኅበራዊ ድርጅቶች፣ የትምህርት ተቋሞችና ለንግድ ሥራ ድጋፍ የሚሰጡ በርካታ አካላትን አቅም የመገንባት ሥራ አከናውኗል። በኢትዮጵያም ሆነ በመላው አውሮፓ በትምህርት ተቋሞች፣ በዩኒቨርሲቲዎችና በቴክኒክ እና የሙያ ማሰልጠኛ ተቋሞች መካከል አጋርነት እንዲፈጠር ድጋፍ በመስጠት ማኅበራዊ ተቋሞች ሥራ ቀጣሪዎችና ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ የሚያስፈልጉትን ክህሎቶች የማስተማርን አስፈላጊነት ለትምህርት ተቋሞች ለማሳየት እንጥራለን።

በአገር፣ በክልልና በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተሳሰርና የአጋርነት መድረኮችን በመፍጠር የማኅበራዊ ተቋም ዘርፍ ያለውን ሊጎለብት የሚችል አቅም በሰፊው የማሳየት ግብ አለን፤ ይህንንም የምናደርገው ኢትዮጵያ ውስጥ የመማር አጋጣሚዎችን በመክፈትና ማኅበራዊ ተቋሞች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ አዳዲስ ገበያዎችን በማፈላለጉ ሥራ እርዳታ በማበርከት ነው። ይህን ማድረግ ገንዘብ ለጋሾችና ለማኅበራዊ ጉዳዮች መዋዕለ ነዋይ የሚያፈሱ ሰዎች ገንዘብ ለመስጠት እንዲነሳሱ በመርዳት ዘርፉ ተጨማሪ ካፒታል እንዲገኝ ያስችላል።

አድራሻ

ዉበት ግርማ
ሪጅናል ቲም ሊደር
ኢሜይል፦ Wubet.Girma@et.britishcouncil.org

ብሪቲሽ ካውንስል ኢትዮጵያ
ስልክ፦ +251 (0)116174300 / 116620388
ኢሜይል፦ Information@et.britishcouncil.org
https://www.ethiopia.britishcouncil.org

https://www.facebook.com/BritishCouncilEthiopia/

ብሪቲሽ ካውንስል ኬንያ
ስልክ፦ +254 (0)202836000
ኢሜይል፦ information@britishcouncil.or.ke
https://www.britishcouncil.co.ke/

https://www.facebook.com/BritishCouncilKenya