ኮርሱን በተመለከተ

የምንሰጣቸው መደበኛ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ኮርሶቻችን የቋንቋ ችሎታዎን በሁሉም አቅጣጫ እንዲያሻሽሉ ለመርዳት የተዘጋጁ ናቸው። እያንዳንዱ ትምህርት ግልጽ የሆነ ዓላማ ያለው ሲሆን ለሚያደርጉት አጠቃላይ መሻሻል የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፤ ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ያወጧቸው ግቦች ላይ እንዲደርሱም ይረዳዎታል።

በእያንዳንዱ ክፍል አስተማሪዎ በሚገባ የተደራጁ የመማሪያ ሥራዎችን ይሰጥዎታል፤ እድገትዎንም ይከታተላል። እንዲሁም እንግሊዝኛ ቋንቋን ይበልጥ አቀላጥፈው እና በድፍረት መናገር እንዲችሉ ሐሳብ ይሰጥዎታል።

ለምን ይህን የብሪቲሽ ካውንስል ኮርስ ልምረጥ?

ይህ መደበኛ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ኮርስ የሚያስገኝልዎ ጥቅም፦

  • ብቃት እና ልምድ ያለው አስተማሪ ያስተምርዎታል፣
  • ሐሳብዎን የመግለጽ ችሎታዎን ያሻሽላሉ፣
  • በድፍረት የመናገር ችሎታ ያዳብራሉ፣
  • ቃላትን በትክክል የመጥራት ችሎታዎን ያሻሽላሉ፣
  • የሰዋስው እና የቃላት እውቀትዎን ያሰፋሉ፣
  • በመማሪያ ክፍል ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጪ የእንግሊዝኛ ችሎታዎን ለማሻሻል የሚረዱ የተለያዩ ዘዴዎች ያውቃሉ፣
  • የሚያደርጉትን ጥረት በተመለከተ ሐሳብ ያገኛሉ፣
  • ኮርሱን በተሳካ ሁኔታ ካጠናቀቁ የምሥክር ወረቀት ይሰጥዎታል።

የእርስዎ ትክክለኛ የቋንቋ ደረጃ

መደበኛ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ኮርሶች እንሰጣለን፤ ይህም የመናገር፣ የመስማት፣ የማንበብ እና የመጻፍ ችሎታዎንም ሆነ የሰዋስው እና የቃላት እውቀትዎን እንዲያሳድጉ ይረዳዎታል። ኮርሶቹ ከጀማሪ ደረጃ አንስቶ እስከ ከመካከለኛ ከፍ ያለ ደረጃ ይደርሳሉ።

በብሪቲሽ ካውንስል አዲስ ተመዝጋቢ ከሆኑ ለእርስዎ የሚመጥነው ትክክለኛ ደረጃ የትኛው እንደሆነ ለማወቅ የምደባ ፈተና መውሰድ ይኖርብዎታል።

ችሎታዬ የሚገመገመው እንዴት ነው? 

ያደረጉትን ለውጥ የምንመዝነው ቀጣይነት ባለው ግምገማ ነው።

ይህን የምናደርገው ምን ጠንካራ ጎኖች እንዳሉዎት እና በምን አቅጣጫ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብዎት እንዲገነዘቡ ለመርዳት ነው። ከዚህም ሌላ ወደ ቀጣዩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ደረጃ ለመሸጋገር ብቁ መሆንዎን ለመወሰን እንዲረዳን ያሳዩትን ለውጥ እንገመግማለን።

በቀጣይነት የሚደረገው ግምገማ በሙሉ የተመሠረተው ተግባራዊ በሆኑ መገምገሚያ ስልቶች ነው።

ትምህርቱ የሚሰጠው የት ነው?

አዲስ አበባ

የስልጠና ቀናት እና የክፍያ ተመኖች

አዲስ ተማሪ ከሆኑ የምደባ ፈተና መውሰድ ይኖርብዎታል፤ ይህም ትክክለኛው ደረጃ ላይ እንድንመድብዎት ያስችለናል። 

ምን፦

የምደባ ፈተና የሰዋስው እና የቃላት እውቀትን እንዲሁም የንባብ እና የንግግር ችሎታን ያጠቃልላል።  

መቼ፦

ረቡዕ እና ዓርብ (13.00 - 14.30) (ከቀኑ 7.00 – 8.30) 

የሚፈጀው ጊዜ፦

90 ደቂቃ

የክፍያው መጠን፦

200 ብር

እባክዎ የእንግሊዝኛ ችሎታዎትን ደረጃ ማወቅ እንዲችሉ ለምንሰጠው ፈተና ለመመዝገብ በ +251 116 174 300/ +251 911 512 835 ስልክ ቁጥር ይደውሉልን።

ትምህርቱን የሚመለከት መረጃ 

ምን፦

ጀማሪ፣ የመጀመሪያ ደረጃ፣ ቅድመ መካከለኛ ደረጃ፣ መካከለኛ ደረጃ፣ ከመካከለኛ ከፍ ያለ ደረጃ

የሚፈጀው ጊዜ፦

በአሥር ሳምንታት ውስጥ ለ60 ሰዓታት

የክፍያው መጠን፦

5550 ብር እና 1050 ብር ለመማሪያ መጽሐፍ 

ከ500 ብር በላይ የሆነ ክፍያ በሙሉ ክፍያዎትን በቀላሉ በቀጥታ ወደ ባንክ አካውንታችን ገቢ ማድረግ ይችላሉ (የክፍያ አፈጻጸም መመሪያውን በዚህ ገጽ ላይ ያንብቡ) ወይም በጥሬ ገንዘብ ክፍያ ማዘዣ (CPO) በየትኛውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በኩል ገንዘቡ ለብሪቲሽ ካውንስል እንዲከፈል ገቢ ማድረግ ይቻላል። ቦታ እንዲያዝልዎ የኮርሶቹን ሙሉ ዋጋ መክፈል ይጠበቅብዎታል። ከሰኞ እስከ ዓርብ ከቀኑ11፡00 በኋላ እና ቅዳሜ ደረሰኝ እና ቼክ እንዲሁም ክፍያ መቀበልን የመሳሰሉ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን እንደማናስተናግድ እባክዎ ያስታውሱ።

ኮርሱ የሚፈጀው ጊዜ

የጠዋት ፈረቃ የሚኖረው በሳምንት ሁለት ጊዜ (በቀን ለ3 ሰዓታት) ሲሆን፤ የከሰዓት በኋላ እና የማታ ፈረቃ ደግሞ በሳምንት ሦስት ጊዜ (በቀን ለ2 ሰዓታት) ይኖራል።  

የበጋ የስልጠና መርሃ ግብር 

የጠዋት ክፍለ ጊዜ ስልጠናዎች  

የትምህርት ዓይነት  ቀን ሰዓት 
     
የጠዋት የትምህርት መርሃ ግብር

ህዳር 26 - የካቲት 11 2011

ሰኞ እና ረቡዕ 09.15 - 12.15 (ከጠዋቱ 3፡15 እስከ 6፡15) 

ማክሰኞ እና ሐሙስ 09.15 - 12.15 (ከጠዋቱ 3፡15 እስከ 6፡15) 

     

የከሰዓት በኋላ እና የምሽት የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች    

መደበኛ የእንግሊዝኛ ቋንቋ በሳምንት ሦስት ቀን  ከህዳር 26 - የካቲት 11 2011 ሰኞ፣ ረቡዕ እና ዓርብ 16.15 - 18.15 ወይም 18.30 - 20.30 (ከቀኑ 10፡15 – 12፡15 ወይም ከምሽቱ 12፡30 – 2፡30) 
መደበኛ የእንግሊዝኛ ቋንቋ በሳምንት ሦስት ቀን  ከህዳር 26 - የካቲት 11 2011 ማክሰኞ፣ ሐሙስ እና ቅዳሜ - 16.15 - 18.15 ወይም 18.30 - 20.30 (ከቀኑ 10፡15 - 12፡15 ወይም ከምሽቱ 12፡30 – 2፡30 (ቅዳሜ 14.00 - 16.15 [ከቀኑ 8፡00 – 10፡15] በተከታታይ) 

ክፍያ ከፈፀሙ በኋላ መማር የማይችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር ኮርሱ ከሚጀምርበት ቀን በፊት የከፈሉት ገንዘብ ሙሉ በሙሉ እንዲመለስልዎት ወይም ለሌላ ጊዜ እንዲዘዋወርልዎት መጠየቅ ይችላሉ፤ በዚህ ጊዜ ለቢሮ ሥራ የሚከፈል 550 ብር ተቀናሽ ይሆናል። ኮርሱ ከጀመረ በኋላ የከፈሉትን ገንዘብ ማስመለስ ወይም ለሌላ ጊዜ ለመጠቀም ማዘዋወር አይቻልም፤ ከዚህ የተለየ ሁኔታ የሚኖረው የትምህርት አስተዳደሩ የተስማማባቸው ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሲኖሩ ለምሳሌ፣ ድንገተኛ የሕክምና ጉዳይ በሚከሰትበት ወቅት በሚያቀርቡት ማስረጃ መሰረት ገንዘብ የማስመለስ/ ለሌላጊዜ የማዛወር ሥራ ሊካሄድ ይችላል።

ብሪቲሽ ካውንስል፣ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ባልተጠበቁ ክስተቶች ሳቢያ የትምህርት መርሃ ግብሩን ለመሰረዝ የሚገደድባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የፈፀሙትን ክፍያ ሌላ ኮርስ እንዲወስዱበት ወይም ወደፊት እንዲማሩበት ልናደርግ እንችላለን። ይህ የማይቻል ከሆነ ግን የከፈሉትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ እንመልሳለን።

ኮርሱ መሰጠት ከጀመረበት ቀን ጀምሮ የከፈሉትን ገንዘብ ማስመለስ ወይም ለሌላ ጊዜ እንዲዘዋወር ማድረግ አይቻልም።