ፈተና በጣም የተረጋጉ በሚባሉ ተማሪዎችም ላይ ሳይቀር ተጨማሪ ጫና ይፈጥራል። ይሁንና የተወሰነ ዝግጅት በማድረግና የታሰበበት ፕሮግራም አውጥቶ ትምህርቱን በመከለስ የሚገባዎትን ውጤት ማግኘት ይችላሉ።

ተማሪም ሆኑ አስተማሪ ከብሪቲሽ ካውንስል ጠቃሚ የሆኑ በርካታ መጽሐፎችና መማሪያዎችን ማግኘት ይችላሉ። በተጨማሪም የሚከተሉትን ጠቃሚ ምክሮች ልናካፍልዎት እንወዳለን፦

የፈተናው ቀን ከመድረሱ ከሁለት ወር በፊት፦

አሁን ክለሳ የሚያደርጉበትን ፕሮግራም ስለማውጣት በቁም ነገር ማሰብ መጀመር ይኖርብዎታል። የሚከተሉትን ነገሮች ያድርጉ፦

  • ለእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት የተዘጋጀውን ወቅታዊ ሥርዓተ ትምህርት ፈልገው ያግኙ
  • ፈተናውን በተመለከተ አንዳንድ መረጃዎች ለማግኘት ይሞክሩ (ለምሳሌ ያህል፣ ጥያቄዎቹ ምርጫ ናቸው ወይስ በተጻፉ ነገሮች ላይ የተመሠረቱ?)
  • ክለሣ የሚያደርጉበትን ፕሮግራም ያዘጋጁ።

ለክለሣ የሚጠቅሙ አንዳንድ ሐሳቦች፦

የተማሩትን የሚከልሱበት ፕሮግራም ሲያወጡ ከቀኑ ውስጥ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆኑበትን ጊዜ ይምረጡ። ለምሳሌ ያህል፣ ጠዋት ላይ ቀለል የሚልዎትና ነቃ የሚሉ ከሆነ ሰፊ ጊዜ መድበው ከማጥናት ወደኋላ አይበሉ። ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ለማድረግም ጥረት ያድርጉ፦

  • በአንድ የትምህርት ዓይነት ብዙ ነጥብ ለሚይዙ የፈተና ዓይነቶች ቅድሚያ ይስጡ፣
  • አእምሮዎን ለማደስ አዘውትረው የተወሰነ እረፍት ያድርጉ፣
  • መጽሐፎችን፣ በድምፅ የተቀዱ መመሪያዎችንና ኢንተርኔት ላይ የሚገኙ በቪዲዮ የቀረቡ ዋና ዋና ሐሳቦችን ጨምሮ ለማጥናት የሚረዱ የተለያዩ ዝግጅቶችን ተጠቅመው ትምህርቱን ይከልሱ፣
  • ሲያጠኑ በያዙት ማስታወሻ ላይ ቁልፍ ነጥቦችን ያስምሩባቸው፣
  • ከእያንዳንዱ ርዕስ ጋር በተያያዘ የቤተሰብዎ አባል ወይም ጓደኛዎት የሆነ ሰው ጥያቄዎች እንዲጠይቅዎት ያድርጉ፣
  • የጥያቄዎቹን ዓይነትና የሚመደበውን ሰዓት በተመለከተ ግንዛቤ ማግኘት እንዲችሉ የድሮ ፈተናዎችን ይሥሩ፣
  • ከቤተሰብዎ እና ከጓደኞችዎ ጋር ዘና የሚሉበት ጊዜ ይመድቡ።

ከፈተናው ቀን ከአንድ ወር በፊት፦

በትምህርት ቤትዎ በኩል የሚፈተኑ ተማሪ ከሆኑ የፈተና አስተባባሪው የመፈተኛ ፈቃድ ያገኙበትን ወረቀት ይሰጥዎታል። ወረቀቱ ፈተና የሚፈተኑበትን ትክክለኛ ቀን ይገልጻል፤ ይህም ወደ ቦታው ለመሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ያስችልዎታል። በፈተናው ቀን ይህን ቅጽ ይዘው መምጣት አይዘንጉ።

ለፈተና ምን ይዘው መምጣት እንደሚያስፈልግዎትና የፈተና ፕሮግራሙን መመልከት እንዲችሉ የሚፈተኑበት ቀን የሚለውን ይመልከቱ።

እስከዚያው ጊዜ ድረስ ባወጡት ፕሮግራም መሠረት ክለሳ ማድረግዎትን ይቀጥሉ፤ ይሁንና ጉልበትዎ እንዳይሟጠጥ የእረፍት ጊዜ የመመደብን አስፈላጊነት አይዘንጉ።

ለፈተና ቀን የሚጠቅሙ ሐሳቦች

እንግዲህ ጥናትዎንና ዝግጅትዎን አጠናቅቀው ለቁርጥ ቀን ተዘጋጅተዋል። የመረበሽ ስሜት ቢሰማዎት ግራ አይጋቡ፤ ይሄ ያለ ነገር ነው። ዘና ለማለትና በተቻለ መጠን ጥሩ ውጤት ለማምጣት የሚከተሉትን ጥቂት ተጨማሪ ምክሮች ተግባራዊ ያድርጉ፦

  • ለመረጋጋት ይሞክሩ እንዲሁም ደጋግመው በደንብ ይተንፍሱ፣
  • ፈተናውን መሥራት ከመጀመርዎ በፊት የጥያቄ መረቀቱን ከዳር እስከ ዳር ያንብቡ፣
  • የተመደበውን ጊዜ ይከፋፍሉ፣
  • ከባድ ጥያቄ ሲያጋጥምዎት ወደሚቀጥለው ይለፉ፣
  • ጥያቄዎቹን በጥሞና ያንብቡ፣ ለእያንዳንዱ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ መስጠትዎን እርግጠኛ ይሁኑ፣
  • ፈተናውን በሚሠሩበት ወቅት አልፎ አልፎ ውኃ ይጎንጩ፣
  • በተለይ ፈተናውን በጊዜ ሠርተው ከጨረሱ የጻፏቸውን መልሶች ተመልሰው ይመልከቱ።

በጽሑፍ ላይ ለተመሠረቱ ጥያቄዎች የሚሰጧቸው መልሶች የመጀመሪያ፣ የመካከለኛና የመጨረሻ ክፍል ባለው መንገድ መዋቀር እንደሚኖርባቸው ያስታውሱ። የመጀመሪያው ክፍል የጽሑፉ መግቢያ ነው፤ መካከለኛው ደግሞ ርዕሰ ጉዳዩ በዝርዝር የሚብራራበት ክፍል ሲሆን ከአጠቃላዩ የቃላት ብዛት ውስጥ 75 ከመቶ ገደማ መያዝ ይኖርበታል። በሌላ በኩል የመጨረሻው ክፍል ጽሑፉ የሚቋጭበት ወይም ፍሬ ሐሳቦቹ ጠቅለል ተደርገው የሚቀርቡበት ነው።