አንዳንድ ጊዜ ተፈታኞች የጠበቁትን ያህል ውጤት አያገኙም። እርስዎም እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመዎት ብዙም ባይጨነቁ ጥሩ ነው። ያገኙት ውጤት ተጨማሪ ትምህርት እንዲማሩ ወይም የሥራ እድሎችን እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሌሎች አስደሳች አጋጣሚዎችን ሊፈጥርልዎት ይችላል። ይሁንና በአንዳንድ ምክንያቶች ለምሳሌ አስተማሪዎ ከፍተኛ ውጤት እንደሚያገኙ ገምቶ ከነበረ ውጤትዎ እንዲስተካከል ለመጠየቅ ወይም እንደገና ለመፈተን ሊያስቡ ይችላሉ።
በድጋሚ መፈተን እና ውጤት ማስተካከል
በድጋሚ መፈተን
እርስዎ ወይም አስተማሪዎ የተሻለ ውጤት ሊያገኙ እንደሚችሉ ካሰባችሁ እንደገና መፈተን ይችላሉ።
በድጋሚ መፈተን ማለት ምን ማለት ነው?
ባለፈው አመት ያንኑ ፈተና ተፈትነው ከነበረ ፈተናውን በድጋሚ እንደመፈተን ይቆጠራል።
የ2014 (እ. ኤ. አ.) የካምብሪጅ ኢንተርናሽናል ኤግዛሚኔሽንስ (CIE) ተማሪዎች እንደገና ለመፈተን ማመልከቻ ማቅረብ የሚችሉበት ቀን የሚያበቃው መስከረም 21 ቀን 2014 (እ. ኤ. አ.) ነው።
ምን ማድረግ አለብዎት?
በትምህርት ቤትዎ በኩል የሚፈተኑ ተማሪ ከሆኑ የትምህርት ቤቱን የፈተናዎች አስተባባሪ ማነጋገር አለብዎት። የግል ተማሪ ከሆኑ ከዚህ በታች የተገለፁትን ነገሮች ማቅረብ አለብዎት፦
- የቀድሞ ትምህርት ቤትዎን መለያ ቁጥር
- የተፈታኝ መለያ ቁጥርዎን
- በድጋሚ በፕሮግራሙ እንዲካፈሉ የተሰጠዎትን ፈቃድ።
ማሳሰቢያ፦ በድጋሚ ሊካፈሉባቸው የማይችሏቸው ፕሮግራሞች ሊኖሩ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ፣ ከዚህ ቀደም የሠሯቸውን ሥራዎች በማቅረብ የጽሑፍ ፈተናውን ብቻ መፈተን ይችላሉ። በድጋሚ የቀረቡት ሁሉም ሥራዎች፣ በአዲሱ የፈተና ቅደም ተከተል ፕሮግራም ላይ ካሉት ነገሮች ጋር መስማማት አለባቸው፤ እንዲሁም እንደገና መገምገም ይኖርባቸዋል።
ውጤት ማስተካከል
እያንዳንዱ የፈተና ወረቀት በተቆጣጣሪዎች ቡድን ይገመግማል። የቡድኑ አባላት በሚያስተምሩት የኮርስ አይነት ረገድ ባለሙያዎች ሲሆኑ ጥብቅ የሆነ የውጤት አሰጣጥ ዘዴ ይጠቀማሉ። ዋና ተቆጣጣሪዎች በአግባቡ ውጤት እንደተሰጠ ለማረጋገጥ፣ ግምገማውን በበላይነት ይመራሉ።
አንድ ተማሪ ያገኘው ውጤት አስተማሪው ከገመተው ወይም በንፅፅር ካስቀመጠው በእጅጉ የተለየ ከሆነ ውጤቱ ወዲያውኑ እንዲጣራ ይደረጋል፤ ይህ ከሆነ በኋላ በአብዛኛው ውጤቱ እንዲስተካከል ይደረጋል። ወይም ደግሞ ትክክለኛ ደረጃ እንዲሰጥ አማካኝ ውጤቶችም ጭምር ይስተካከላሉ።
የፈተና ውጤት አሰጣጥ ሂደቱ፣ ሁሉም ተማሪዎች የሚገባቸውን ውጤት እንዲያገኙ ሲባል በጥንቃቄ የተዘጋጀ ነው። ይሁንና የተሰጠዎት ውጤት ለሠሩት ሥራ የማይመጥን እንደሆነ ከተሰማዎት ውጤትዎ እንዲስተካከልልዎት መጠየቅ ይችላሉ።
ውጤት እንዲስተካከል መጠየቅ
በትምህርት ቤት በኩል የተፈተኑ ተፈታኝ ከሆኑ እና የተሳሳተ ውጤት እንዳገኙ ከተሰማዎት ከአስተማሪዎት ጋር መነጋገር ይገባዎታል። አስተማሪዎት ውጤት እንዲስተካከልልዎት መጠየቅ እንዳለብዎት ከተስማማ ጉዳዩን ለትምህርት ቤትዎ ማሳወቅ አለብዎት። በዚህ ጊዜ ከአስተማሪዎ የድጋፍ ደብዳቤ ማግኘት ሊኖርብዎት ይችላል፤ ብዙውን ጊዜ፣ ውጤት ለማስተካከል ክፍያ ሊጠየቁ ይችላሉ።
የግል ተፈታኝ ከሆኑ፣ በሰኔ 2014 (እ. ኤ. አ.) ለነበረው የፈተና ክፍለ ጊዜ ከመስከረም 30 ቀን 2014 (እ. ኤ. አ.) በፊት ባሉት ጊዜያት፣ በኅዳር 2014 (እ. ኤ. አ.) ለነበረው የፈተና ክፍለ ጊዜ ደግሞ ከየካቲት 26 ቀን 2015 (እ.ኤ.አ.) በፊት ባሉት ጊዜያት ብሪቲሽ ካውንስልን ማነጋገር አለብዎት።
የካምብሪጅ ኢንተርናሽናል ኤግዛሚኔሽንስ (CIE) እና የፒርሰን ኤዴክሴል ተፈታኞች ውጤትን የሚመለከት ጥያቄ ማቅረቢያ ቅፅ ከብሪቲሽ ካውንስል የፈተናዎች አገልግሎት መስጫ ክፍል ማግኘት ይችላሉ።
ያስታውሱ፦ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ውጤትዎ ተመርምሮ ከነበረበት ዝቅ ሊል፣ በነበረበት ሊፀና ወይም ከፍ ሊል ይችላል። ውጤትዎ ከፍ ካለ ይህንን አገልግሎት ለማግኘት የከፈሉት ክፍያ ሙሉ ለሙሉ ተመላሽ ሊደረግልዎት ይችላል።
አስተማሪዎች እና የፈተና ጉዳይ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት፣ የፈተና ውጤት እንዲስተካከል ከመጠየቃቸው በፊት የተፈታኙን ፈቃድ ማግኘት አለባቸው። የፒርሰን ኤዴክሴል ተፈታኝ ከሆኑ፣ የተፈታኞችን የስምምነት ቅፅ መሙላት ይገባዎታል፤ ቅፁን ከዚህ ገጽ ላይ ማውረድ ይችላሉ።
የቡድን ሪፖርቶች
አስተማሪዎች የአንዱን የተፈታኞች ቡድን ወይም ደግሞ የሁሉንም ተማሪዎች የፈተና ውጤት የሚመለከት ዝርዝር ሪፖርት እንዲቀርብላቸው ማዘዝ ይችላሉ።
ብሪቲሽ ካውንስል እስከ አምስት፣ እስከ 15፣ እስከ 16 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ቡድኖችን ሪፖርት እንዲጠይቁ ይፈቅድልዎታል።
የፈተና ሪፖርት እንዲሰጥዎት ማዘዝ ከፈለጉ ከእያንዳንዱ ተማሪ የጽሑፍ ፈቃድ ማግኘት አለብዎት።