IELTS Academic - ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም ይዘጋጁ

የ IELTS Academic ፈተና ለከፍተኛ ትምህርት የሚፈለግ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የብቃት ደረጃ እንዳለዎት ይለካል። ይህም የአካዳሚክ ቋንቋን አንዳንድ ገጽታዎች ያንፀባርቃል እና ትምህርት ወይም ስልጠና ለመጀመር ዝግጁ መሆንዎን ይገመግማል።

የሚከተሉትን ከፈለጉ ይህንን ፈተና ይውሰዱ፡

 • በየትኛውም የዓለም ክፍል በመጀመሪያ ዲግሪ ወይም በድህረ ምረቃ ትምህርት ደረጃ ትምህርት ለመከታተል ከፈለጉ
 • በዩኬ ውስጥ በ Tier 4 ስፖንሰር በሆነ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለ Tier 4 የተማሪ ቪዛ ለማመልከት ከፈለጉ
 • በእንግሊዝኛ ተናጋሪ አገራት ውስጥ በሙያዊ ድርጅት ውስጥ ለመስራት።  

IELTS ለ UKVI (ቪዛዎች እና ኢሚግሬሽን) እንዲወስዱ ወደ ጠየቅዎት የዩኬ ዩኒቨርሲቲ እያመለከቱ ከሆነ። ስለ IELTS ለUKVI የበለጠ ይወቁ

የ IELTS Academic ክፍያዎች፡ 183 ፓውንድ (10,400.00 ብር)

ዋጋው ምን ያካተተ ነው? የIELTS ዋጋችን የተመረጡ ጠቃሚ ፈተና መዘጋጃ ስልጠናዎችን፣ ነጻ የመለማመጃ ፈተናዎችንና ሌሎች ግብዓቶችን ያካተተ ነው።  

የጊዜ ርዝመት፡ 2 ሰዓት እና 45 ደቂቃዎች (ማንበብ፣ ማዳመጥ፣ መጻፍ) + 11-14 ደቂቃ ለንግግር ፈተና

ቅርጸት፡ ለፈተናው አራት ክፍሎች አሉ፡ ማዳመጥ፣ ማንበብ፣ መጻፍ እና መናገር። የ IELTS ፈተናዎን ለመውሰድ በብሪቲሽ ካውንስል ቦታ ሲይዙ ፈተናው በኦፊሴላዊ የብሪትሽ ካውንስል IELTS ፈተና ማእከል ውስጥ ይከናወናል።

የንግግር ፈተናዎ እንደ ሌሎቹ የፈተና ክፍሎች በተመሳሳይ ቀን፣ ወይም ከሌሎች ፈተናዎች በፊት ወይም በኋላ እስከ አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሊሰጥ ይችላል። የንግግር ፈተናዎ ከዋናው ፈተናዎ በተለየ ቀን ውስጥ የሚሆን ከሆነ አስቀድሞ ማሳወቂያ ይደርስዎታል።

 

IELTS Academic ፈተና ክፍል 1፡ የማዳመጥ ተግባሮች

የጊዜ ርዝመት፡ 30 ደቂቃዎች እና 10 ደቂቃ ምላሾችዎን ወደ መልስ መስጫው ሉህ ለማስተላለፍ

ቅርጸት፡ አራት የድምፅ ቅጂዎች በተለያየ ዘዬዎች።  

መልሶችዎን የሚከተሉትን በመጠቀም ይጽፋሉ፡  

 • ብዙ ምርጫ
 • ማዛመድ
 • የስዕል ማብራሪያ
 • ዓረፍተ ነገር ማጠናቀቅ።

አራት የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎችን ድምጾች ቅጂ ያዳምጡ እና ከዚያም ለበርካታ ጥያቄዎች መልሶችዎን ይጽፋሉ።

 • ቅጂ 1 – በዕለት ተዕለት ማህበራዊ አውድ የተዘጋጀ በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ ውይይት።
 • ቅጂ 2 – በዕለት ተዕለት ማህበራዊ አውድ የተዘጋጀ የአንድ ሰው ንግግር፣ ለምሳሌ፡ ስለ አካባቢያዊ መገልገያዎች ንግግር።
 • ቅጂ 3 – በትምህርታዊ ወይም የሥልጠና አውድ የተዘጋጀ እስከ አራት በሚደርሱ ሰዎች መካከል የሚደረግ ንግግር፣ ለምሳሌ፡ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ እና አንድ ተማሪ ስለ አሳይንመንት ሲወያዩ።
 • ቅጂ 4 – በአንድ የትምርት ዓይነት ላይ የሚደረግ የአንድ ሰው ንግግር፣ ለምሳሌ፡ የዩኒቨርሲቲ ሌክቸር።

ገምጋሚዎች ዋና ዋናዎቹን ሃሳቦች እና ዝርዝር የእውነታ መረጃዎችን፣ የተናጋሪዎች አስተያየቶች እና አመለካከቶችን፣ የአንድን ቃል ዓላማ እና የሃሳቦችን እድገት የመከታተል ችሎታዎን ለመረዳት ማስረጃዎችን የሚፈልጉ ይሆናል።

IELTS Academic ፈተና ክፍል 2፡ የማንበብ ተግባራት

የጊዜ ርዝመት፡ 60 ደቂቃ

ቅርጸት፡

 • ሶስት ረጃጅም የንባብ ምንባቦች ከተግባራት ጋር (ምስሎችን፣ ግራፎችን ወይም ስዕሎችን ጨምሮ)
 • ጽሑፎች ከገላጭ እና እውነታዎች እስከ ዲስኩር እና ትንታኔያዊ ይደርሳሉ።

የንባብ ክፍሉ በርካታ የማንበብ ክህሎቶችን ለመመዘን የተቀረጹ 40 ጥያቄዎችን ይይዛል። እነዚህም ለጭብጥ ማንበብ፣ ዋነኞቹን ሀሳቦች ለመረዳት ለማንበብ፣ ለዝርዝር ማንበብ፣ ምክንያታዊ የሆኑ ክርክሮችን ለመረዳት እና የጸሐፊዎችን አመለካከት፣ ዝንባሌ እና ዓላማ መገንዘብን ያካትታሉ።

ይህ ክፍል ዕውነታዊ መረጃ እስከ መወያያ ጽሁፎች እና ትንታኔዎች የሚደርሱ ሦስት ረጃጅም ፅሁፍዎችን ያካትታል። እነዚህም ከመጻሕፍት፣ ጆርናሎች፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች የሚወሰዱ ናቸው። ልዩ ላልሆኑ ተሳታፊዎች የተመረጡ ሲሆን ነገር ግን የዩኒቨርሲቲ ኮርሶችን ለሚጀምሩ ሰዎች ወይም ሙያዊ ምዝገባ ለሚፈልጉ ሰዎች ተገቢ ናቸው።

IELTS Academic ፈተና ክፍል 3፡ የመጻፍ ተግባሮች

የጊዜ ርዝመት፡ 60 ደቂቃ

ቅርጸት፡

 • ጽሁፍ ወይም ንድፎችን ለመግለፅ፣ ለማብራራት ወይም ለማጠቃለል አንድ የጽሁፍ ተግባር (ቢያንስ 150 ቃላት)
 • አንድ የድርሰት ተግባር (ቢያንስ 250 ቃላት)።

ርዕሰ ጉዳዮች አጠቃላይ ፍላጎት እና ወደ መጀመሪያ ዲግሪ ወይም የድህረ ምረቃ ትምህርት የሚገቡ ወይም የሙያ ምዝገባ ለሚፈልጉ ተስማሚ ናቸው። ሁለት ተግባራት አሉ፡

 • ተግባር 1 – ግራፍ፣ ሠንጠረዥ፣ ቻርት ወይም ስዕል ይቀርብልዎት እና በራስዎ ቃላት መረጃውን እንዲገልጹ፣ እንዲያጠቃልሉ ወይም እንዲያብራሩ ይጠየቃሉ። መረጃውን እንዲገልጹ እና እንዲያብራሩ፣ የሂደትን ደረጃዎች እንዲገልጹ፣ አንድ ነገር እንዴት እንደሚሰራ ወይም አንድ ነገር ወይም ክስተትን እንዲገልጹ ሊጠየቁ ይችላሉ።
 • ተግባር 2 – ለአንድ አመለካከት፣ ክርክር ወይም ችግር ምላሽ ጽሁፍ እንዲጽፉ ይጠየቃሉ።

IELTS Academic ፈተና ክፍል 4፡ የንግግር ተግባራት

የጊዜ ርዝመት፡ ከ 10 - 14 ደቂቃዎች

ቅርጸት፡

 • ስለ ተለመዱ ርዕሶች አጭር ጥያቄዎችን እና ስለአንድ ርዕስ በዝርዝር ከፈታኝዎ ጋር ፊት ለፊት የሚደረጉ ቃለ መጠይቆች።
 • ልብ ይበሉ፡ እንደ ፈተና ማዕከሉ አካባቢ፣ የፈተናዎን የንግግር ክፍል በተለየ ቀን መያዝ ሊኖርብዎ ይችላል።

የንግግሩ ክፍል የንግግር እንግሊዝኛ ቋንቋን አጠቃቀምዎን ይገመግማል። እያንዳንዱ ፈተና ይቀዳል።

 • ክፍል 1 - ፈታኙ ስለራስዎ እና ስለ ቤት፣ ቤተሰብ፣ ስራ፣ ትምህርት እና ፍላጎቶች ያሉ የተለመዱ ርዕሰ ጉዳዮችን ይጠይቅዎታል። ይህ ክፍል ከአራት እስከ አምስት ደቂቃ ይቆያል።
 • ክፍል 2 - ስለአንድ ርዕስ እንዲናገሩ የሚጠይቅዎ ካርድ ይሰጥዎታል። እስከ ሁለት ደቂቃ ያህል ከመናገርዎ በፊት ለመዘጋጀት አንድ ደቂቃ ይኖርዎታል። ቀጥሎም ፈታኙ በተመሳሳይ ርዕስ ላይ አንድ ወይም ሁለት ጥያቄን ይጠይቃል።
 • ክፍል 3 - በክፍል 2 ውስጥ ስላለው ርዕስ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ይጠየቃሉ። እነዚህም ተጨማሪ ረቂቅ ሀሳቦችን እና ጉዳዮችን ለመወያየት እድል ይሰጥዎታል። ይህኛው የፈተና ክፍል ከአራት እስከ አምስት ደቂቃ ይቆያል።

ለ IELTS Academic ፈተናዎ ቦታ ይያዙ

ስኬት የሚጀምረው ከ IELTS ነው። ግብዎ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መማር ወይም እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆነ አገር ውስጥ መሥራት ከሆነ፣ እንግዲያውስ የ IELTS academic ለእርስዎ ትክክለኛ ፈተና ነው።

በብሪትሽ ካውንስል ውስጥ፣ በፈተናዎ ላይ በደንብ እንዲሰሩ የሚያስችሎትን ድጋፍ ለመስጠት ቁርጠኞች ነን። እኛ ጋር ቦታ በሚይዙበት ጊዜ፣ ነፃ ያልተወሰነ የ Road to IELTS Last Minute ኮርስን ያገኛሉ። ይህም ምክር እና የማጠናከሪያ ትምህርት የሚሰጡ ዘጠኝ ቪዲዮዎችን፣ 100 መስተጋብራዊ ተግባሮችን እና ለአራቱም ክህሎቶች እያንዳንዳቸው ሁለት የ IELTS Academic ልምምድ ፈተናዎችን ያጠቃልላል።

የ IELTS Academic ፈተና ቀንን ያግኙ

ለፈተናዎ ቦታ ከመያዝዎ በፊት ለሚያመለክቱባቸው ድርጅቶች የትኛውን ፈተና እንደሚፈልጉ መፈተሽዎን ያረጋግጡ።